Thursday, July 10, 2025 / Categories: News የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለፌደራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት አቀረበ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለፌደራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት በቀን 02/11/2017 ዓ.ም አቅርቧል፡፡ የዳሰሳ ጥናቱ ዓላማ በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የእውቀት፣ ክህሎት እና ሙያዊ አመለካከት ክፍተቶች ካሉ በዳሰሳ ጥናት በመለየት ለዳኞች የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ለመስጠት እና የዳኞችን የስልጠና ፍላጎት ለመለየት ነው፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ጥናቱ ዳኞች በጉዳዩ ዙሪያ ያላቸውን የስልጠና ፍላጎት አመላካች እንደመሆኑ ከስልጠና ማኑዋል ዝግጅት ቀድሞ ይህ የዳሰሳ ጥናት መቅረቡ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸው የስልጠና ማንዋል ዝግጅቱ በአጭር ግዜ ውስጥ ተዘጋጅቶ ወደ ስልጠናው ቢገባ የተሻለ ውጤት ማስገኘት እንደሚቻል አንስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወ/ሮ ራኬብ መሰለ በበኩላቸው የዳሰሳ ጥናት ሳይካሄድ የሚዘጋጁ የስልጠና ማኑዋሎች በተግባር ያለውን ክፍተት እና የስልጠና ፍላጎት የማያሟሉ በመሆኑ የቀረበው የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት በፓይለት ደረጃ በሚኖሩ ስልጠናዎች እየዳበረ እንደሚሄድ ገልጸዋል፡፡ Previous Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር ዉይይት አደረገ Next Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳኞችና የስራ ኃላፊዎች የአረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ Print 826