Friday, January 31, 2025 / Categories: News የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር የስራ አመራር ቦርድ አባላት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት አደረጉ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር የስራ አመራር ቦርድ አባላት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀን 22/05/2017 ዓ.ም በመገኘት ጉብኝት አድርገዋል፡፡ የቦርድ አባላቱ በቆይታቸው የፌደራል ፍርድ ቤቶችን አጠቃላይ የሪፎርም ስራዎች ላይ ገለጻ የተደረገላቸው ሲሆን በተለይም ፍርድ ቤቶቹ በቴክኖሎጂ ረገድ እየሰሩባቸው ያሉ የለውጥ ተግባራት ላይ ሰፊ ውይይት እንዲሁም ጉብኝት አድርገዋል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት አመራር አባላቱ ፍርድ ቤቱ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማየት መምጣታቸውን አድንቀው ፍርድ ቤቶች አሰራራቸውን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የጀመሩትን ጥረት ከማገዝ አንፃር የዳያስፖራው ማህበረሰብ በቴክኖሎጂ እና እውቀት ሽግግር ተሳትፎ ማድረግ የሚጠበቅበት ከመሆኑም በላይ እንደ ፍርድ ቤት ተገልጋይ በዳኝነት ስርዓቱ ያሉ ጠንካራም ሆነ ደካማ ጎኖች ላይ ግልፅ ግንዛቤ ሊኖረው ስለሚገባ ጉብኝቱ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የማህበሩ የስራ አመራር ቦርድ አባላት በበኩላቸው የፌደራል ፍርድ ቤቶች በቴክኖሎጂ ረገድ እያሳዩ ያለውን ለውጥ አድንቀው የዳኝነት ስርዓቱ መጠናከር እና መሻሻል ሁሉንም አካል የሚጠቅም በመሆኑ የተቋሙን ትክክለኛ ገፅታ ከማስገንዘብ እና አዎንታዊ ለውጦችን ከማጠናከር አንፃር የዲያስፖራው ማህበረሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ መደገፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ Previous Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስርዓት የውጭ አማካሪ ምክር ቤት ዓመታዊ የውይይት መድረክ ተካሄደ Next Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2017 የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት እቅድ አፈፃጸም ሪፖርት ግምገማ ተካሄደ Print 1082