የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ የግብአት ማሰባሰቢያ የምክክር መድረክ ተካሔደ
/ Categories: News

የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ የግብአት ማሰባሰቢያ የምክክር መድረክ ተካሔደ

ላለፉት አስራ አንድ ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን የፍርድ ቤቶች የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ለማሻሻል ተዘጋጅቶ በቀረበ ረቂቅ መመሪያ ላይ ግብአት ለማሰባሰብ የተዘጋጀና የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ጥሪ የተደረገላቸው 160 ያህል ዳኞች፣ ዐቃቢያነ ሕግ፣ ጠበቆች እና ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ተካሔደ፡፡

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ባደረጉት ንግግር የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ማውጣት ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ለዳኞች በህግ የተሰጠ ፍቅድ ሰልጣን ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ እንዲተገበር ለማስቻል መሆኑን እና በዳኞች የሚሰጡ የቅጣት ውሳኔዎች ምክንያታዊነት እ ፍትሃዊነትን ከማፍሰን አንፃር የቅጣት አወሳሰን መመሪያ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ በ2002 ዓ.ም ወጥቶ ሲተገበር ከቆየ በኋላ በ2006 ዓ.ም መሻሻሉን ያስታወሱት ክቡር ፕሬዚደንቱ፣ አሁን በስራ ላይ ያለው መመሪያ ከአስርት ዓመታት በላይ አገልግሎት የሰጠ በመሆኑ መመሪያው በወቅቱ ሲሻሻል ታሳቢ የተደረጉ ሁኔታዎች የተለወጡ በመሆኑና የተለያዩ ትችቶች ሲቀርቡበት የቆየ በመሆኑ መመሪያውን እንደገና ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡

ለውይይት የቀረበው ረቂቅ መመሪያም እስካሁን ሲሰራበት በቆየው መመሪያ ከቅጣቶች መቅለልና መክበድ ጋር በተያያዘ ከባለሙያዎችና ከሕብረተሰቡ ሲቀርቡ የነበሩ ቅሬታዎችን ለማስቀረት፣ በመመሪያው ውስጥ ያልተሸፈኑ የወንጀል ዓይነቶችን ለማካተት፣ በመመሪያው ውስጥ ሊታቀፉ ይገባቸዋል ተብለው የታመነባቸው አዳዲስ ጉዳዮችም እንዲካቱ ለማድረግ ጥረት ስለመደረጉ አንስተዋል፡፡

የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ማሻሻያውን ለማድረግ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ለመለየት መጀመሪያ ጥናት መደረጉና የጥናቱ ውጤትም ማሻሻያውን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመላካች ግኝቶች ያሉት በመሆኑ ይህን መነሻ በማድረግ ዳኞች የተካተቱበት የባለሙያዎች ኮሚቴ እና አማካሪ ተሰይሞ የረቂቅ መመሪያ ዝግጅቱ ሲከናወን ቆይቶ በመድረኩ ተሳታፊዎች ውይይት እንዲደረግበት የቀረበ መሆኑም ታውቋል፡፡

በተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን ረቂቅ መመሪያው ይዘት ላይ በረቂት መመሪያ ዝግጅት አማካሪ ባለሙያው አቶ ብዙነህ ሙሉጌታ ለተሳታፊዎቹ ማብራሪያ ተሳታፊዎቹ በተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍለው በረቂቅ መመሪያው ላይ ያላቸውን አስተያየት በተወካዮቻቸው አማካኝነት ለመድረኩ አቅርበዋል፡፡

በቡድኖቹ እና በተሳታፊዎቹ አማካኝነት በቀረቡ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በኮሚቴ አባላትና በአማካሪው እንዲሁም የኮሚቴው ሰብሳቢ በሆኑት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚደንት በክቡር አቶ ተክሊት ይመስል ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ማጠቃለያ ላይም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ከመድረኩ ከተሳታፊዎቹ የቀረቡ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች የቅጣት አወሳሰን መመሪያውን ጠቃሚ መሆኑን አመልክተው መመሪያውን በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ወደሥራ የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአውሮፓ ሕብረት የዳሰሳ ጥናቱ ሲካሔድ ጀምሮ የረቂቅ መመሪያውን ዝግጅት እና የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኩ እንዲዘጋጅ በገንዘብ በመደገፍ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

Previous Article በከባድና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ የተዘጋጀ ሥልጠና ለፌዴራል እና ክልል ፍርድ ቤቶች ዳኞች ተሰጠ
Next Article የፍርድ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መልካም ስነ ምግባርን በመላበስ የተቋሙን ራዕይ ማሳካት እንደሚገባ ተገለጸ
Print
767