የዳኝነት ስርዓቱን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ፍርድ ቤቱ ከማህበሩ ጋር አብሮ እንደሚሰራ ተገለጸ
/ Categories: News

የዳኝነት ስርዓቱን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ፍርድ ቤቱ ከማህበሩ ጋር አብሮ እንደሚሰራ ተገለጸ

የዳኝነት ስርዓቱን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ፍርድ ቤቱ ከማህበሩ ጋር አብሮ እንደሚሰራ ተገለጸ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስርዓቱን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት በቅርቡ ከተቋቋመው የኢትዮጵያ የፌዴራል ጠበቆች ማህበር ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ ገለጹ፡፡

ክቡር አቶ ሰለሞን ይህን የገለጹት በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው በአዲሱ የፌደራል የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ መሰረት ለተቋቋመው የጠበቆች ማህበር ስራ ማስጀመሪያ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በእንግድነት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡

እየተቋቋመ ያለው የጠበቆች ማህበር ሊሰራቸው ከሚገቡ ተግባራት መካከል የዳኝነት ነፃነትን ማስጠበቅና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ማከናወን የሚጠቀሱ ሲሆን የዳኝነት አካሉ ከማንኛውም አካል ጫና ሲደርስበት የጠበቆች ማህበሩ የተቃውሞ ድምጹን በማሰማት እንዲሁም ለዳኝነት ነጻነት መከበር ሌሎች ተግባራዊ ህጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ያለውን ቁርጠኝነት ሊያሳይ ይገባል በማለት በአጽንኦት መልእክታቸወን አስተላልፈዋል፡፡

የዳኝነት አካሉ በሚያከናውናቸው የሪፎርም ስራዎች በንቃት በመሳተፍ ማህበሩ የዳኝነት አካሉን የመደገፍ እና አብሮ የመስራት ግብ ሊይዝ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ጠበቆች በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ የጎላ ድርሻ እንዳላቸው የተናገሩት ከቡር አቶ ሰለሞን አረዳ፤ ጠበቆች የዜጎችን መብቶች ለማስከበር በፍትህ ስርዐቱ እና ህብረተሰቡ መካከል እንደ ድልድይ በመሆን ያገለግላሉ ብለዋል፡፡

አዲስ የተቋቋመው የጠበቆች ማህበር የህግ ባለሙያዎችን ከመወከል እና ጥቅማቸውን ከማስጠበቅ አልፎ የህግ ሙያ እንዲዳብር፤ ጠበቆች የሙያ ስነምግባር ጠብቀው ሃላፊነታቸውን በመወጣት ህብረተሰቡን አንዲያገለግሉ፤ የህግ ትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ፤ የህግ የበላይነትና የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፤ በአጠቃላይም የህግ ስርዓታችን እንዲያድግና እንዲጎለብት አስተዋጾ የማበርከት ሀላፊነት ተጥሎበታል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 ጠበቆች በሃገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሊባል በሚችል ደረጃ የዜጎች መሰረታዊ ሰብአዊ እና ህገመንግስታዊ መብቶች ሲጣሱ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በማቅረብ መብቱ እንዲከበር ማድረግ የሚችሉበት ስልጣን የተሰጣቸው መሆኑን ያስታወሱት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ፤ በአዲሱ የአስተዳደር ህግ አዋጅ መሰረትም የመንግስት ተቋማትን ተጠያቂ በማድረግ ረገድ ማህበሩ ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑን ባስተላለፉት መልእክት ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም በህግ አውጨው የሚወጡ ህጎች ከህገ-መንግስትና ከዓለምአቀፍ ሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ጋር የማይቃረኑ፤ ደረጃቸውን የጠበቁ፤ እና ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ ለማድረግ የጠበቆች ማህበሩ በህግ አወጣጥ ስርዓት ከህግ ማመንጨት ጀምሮ እስከ ማስጸደቅ ድረስ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚኖርበት መክረዋል፡፡

ነጻና ገለልተኛ ፍርድ ቤት ለህግ የበላይነት!

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ዋና ዋናዎቹ
Next Article የቅድመ መዋቅር ነባራዊ ሁኔታ ትንተና  እና ረቂቅ ተቋማዊ ለዕላዊ መዋቅር ላይ ውይይት ተካሄደ
Print
46