Tuesday, August 3, 2021 / Categories: News የዳኞችን ዕውቀት እና ክሕሎት በማጎልበት የዳኝነት አገልግሎት አሠጣጥን ጥራት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው የዳኞችን ዕውቀት እና ክሕሎት በማጎልበት የዳኝነት አገልግሎት አሠጣጥን ጥራት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው የፌደራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓትን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ላይ ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ከፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለተውጣጡ ዳኞች የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ከሐምሌ 24-25 ቀን 2013 ዓ.ም በራዲሰን ብሉ ሆቴል ተሰጠ፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በሥልጠናው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በተለያዩ የሕግ ዘርፎች የዳኞችን ዕውቀት እና ክሕሎት በማጎልበት የዳኝነት አገልግሎት አሠጣጥን ጥራት ማሳደግ ትኩረት ከተሰጣቸው የማሻሻያ ሥራዎች መካከል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የፌደራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ የአስተዳደር አካላት የሚያወጡት መመሪያ በፍርድ ቤት የመመሪያ አወጣጥ ሒደት የሥነሥርዓት ድንጋጌዎችን ሳይከተል የወጣ መሆኑ ሲረጋገጥ፣ ከአስተዳደር ተቋሙ የሥልጣን ገደብ ውጪ የወጣ ሲሆን ወይም በእርከን ከመመሪያ በላይ ከሆኑ ሌሎች ሕጎች የሚቃረን በሚሆንበት ወቅት በዚህ ዙሪያ ለሚመለከተው ፍርድ ቤት አቤቱታ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በሥልጠናው ላይ 15 የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኞች እና 35 የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች የተሳተፉበት ሲሆን ሥልጠናው በአሠልጣኞች ከተደረገ ማብራሪያ በተጨማሪ በቡድን ውይይት (Group Work) በታገዘ ሁኔታ ተሰጥቷል፡፡ ሥልጠናውን የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምሕርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን አባይ ሲሆኑ አሜሪካን አገር በሚገኘው ኦሃዮ ኖርዘርን ዩኒቨርሲቲ የህግ ፕሮፌሰር ኢሚሪተስ (Professor of Law Emeritus) የሆኑት ፕሮፌሰር ሀዋርድ ፊንቶን ሥልጠናውን ከአሜሪካን አገር በቨርችዋል ዘዴ (በርቀት) በመስጠት ተሳትፈዋል፡፡ የአዋጁ ዓላማ መንግሥታዊ አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት በሕገ-መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ማንኛውም የመንግሥት ባለሥልጣን ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንዲሆንና የአስተዳደር ተቋማትም በሰዎች መብቶችና ጥቅሞች ላይ የሚያስከትሉት አሉታዊ ተጽዕኖ በሕግ የሚገዛ እንዲሆን ለማድረግ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡ በአስተዳደር ተቋማት የውሳኔ አሰጣጥና የመመሪያ አወጣጥ መርሆዎችና ሥነሥርዓት እንዲሁም በአስተዳደራዊ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ቅር የተሰኘ ግለሰብ/አካል የውሳኔዎቹና የመመሪያዎቹ ሕጋዊነት በፍርድ ቤት እንዲታረም የሚደረግበት ሥነሥርዓት አስፈላጊ በመሆኑ አዋጁ መውጣቱም በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡ የአስተዳደር መመሪያ ወይም ዉሳኔ እንዲከለስ አቤቱታ የሚቀርበው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሚሆንና ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔም የመጨረሻ እንደሚሆን በአዋጁ ላይ የተደነገገ ሲሆን የአስተዳደር መመሪያን በተመለከተ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሊቀርብበት እንደሚችልም ለመረዳት ተችሏል፡፡ የሥነሥርዓት አዋጁ የመንግሥት ተቋማት ሕግን ብቻ መሠረት አድርገው እንዲሰሩና በሥራቸው ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን ያስረዱት ዶ/ር ሰለሞን አባይ፣ በመንግሥት ተቋማት ሕግ ከተከበረና ተጠያቂነት ከተረጋገጠ ዲሞክራሲያዊ አሠራርን የሚያሰፍን በመሆኑ ይህ ደግሞ በበኩሉ የሥልጣኔ እና የዘመናዊ መንግሥት ባህርያትን የሚያመጣ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የአስተዳደር ተቋማት የሚሰጡት ውሳኔ እና የሚያወጡት መመሪያ በፍ/ቤት የሚከለስበትን አሠራር የሚደነግግ የአስተዳደር ሥነሥርዓት ሕግ እንዲወጣ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ሲደረግ የነበረው ተከታታይ ጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳክቶ የፌደራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 መውጣቱን ለመረዳት ተችሏል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናውን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት የፍትሕ ፕሮጀክት /Feteh (Justice) Activity in Ethiopia/ በመተባበር አዘጋጅተውታል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት Previous Article የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞችና የአስተዳደር ዘርፍ ክፍል ሃላፊዎች የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ Next Article የዳኞች ሥልጠና ፍትሐዊና ተጠያቂነት ያለባቸው ፍርድ ቤቶችን ለመገንባት እንደሚረዳ ተጠቆመ Print 1462