Saturday, August 7, 2021 / Categories: News የዳኞች ሥልጠና ፍትሐዊና ተጠያቂነት ያለባቸው ፍርድ ቤቶችን ለመገንባት እንደሚረዳ ተጠቆመ የዳኞች ሥልጠና ፍትሐዊና ተጠያቂነት ያለባቸው ፍርድ ቤቶችን ለመገንባት እንደሚረዳ ተጠቆመ በፌደራል በጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በዩ.ኤን.ዲፒ (UNDP) መካካል እየተተገበረ ባለው የፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ፕሮጀክት አማካኝነት እየተካሄደ በሚገኘው የዳኞች ስልጠና ሥርዓት የዳሰሳ ጥናት ላይ የግብአት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረክ ሐምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም በቤስት ዌስተርን ሆቴል ተካሔደ፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ የውይይት መድረኩን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ሥልጠና የዳኝነት ሥርዓቱ ግንባታ መሠረታዊ አካል መሆኑን ጠቅሰው የዳኞች ሥልጠና ፍትሐዊና ተጠያቂነት ያለባቸው ፍርድ ቤቶችን ለመገንባት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ዘርፉን ለማዘመን እና አሠራሩን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የሶስት ዓመታት የሪፎርም ዕቅድ በማዘጋጀት የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች እያከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰው ከእነዚህ ውስጥ የዳኞችን የሥልጠና ሥርዓት ማጠናከር አንደኛው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ለዳኞች ብቻ የተዘጋጀ ወጥ የሆነ ያልተቆራረጠ፣ ተከታታይነት ያለው የሥልጠና ሥርዓት በተለይም በዳኝነት ሥልጠና ላይ ብቻ ያተኮረ ማዕከል ወይም ተቋም አለመኖሩ እና ለዳኞች ሥልጠና ወጥ እና የታወቀ የጊዜ ሰሌዳ አለመኖሩ እንደተግዳሮት ሲነሳ የቆየ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ የዳኝነት ሥልጠና ዓላማ ዳኞች ፍትሐዊ ፍርድ ለመስጠት ዕውቀታቸውን ለማጎልበት ብቻ ሳይሆን መልካም ስብዕናን የተላበሱ እንዲሆኑ የሚያደርግ ሊሆን ይገብል ያሉት ክቡር ም/ፕሬዚደንቱ፣ በተለይም ወጣት ዳኞች ፍርድ ቤቱን በሚቀላቀሉበት ወቅት ከዕውቀት በተጨማሪ በቂ ክህሎትና የተሟላ ስብዕና እንዲኖራቸው ለማስቻል በበቂ ሥልጠና ውስጥ እንዲያልፉ ማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡ ለውይይት የቀረበው የዳሰሳ ጥናት ዋና ዓላማ የፌደራል ዳኞችን የሥልጠና ፍላጎቶች መለየት ሲሆን የዳሰሳ ጥናቱን ግኝቶች መነሻ በማድረግ ለሚቀጥሉት ዓመታት የሚያገለግል የፌደራል ዳኞች የሥልጠና መርሐ-ግብሮችን፣ ካሪኩለሞችንና ካሌንደሮችን ለመቅረጽ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በውይይቱ ላይ የሶስቱም የፌደራል ፍርድ ቤቶች አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው ዳኞች እንዲሁም የፌደራል የፍትህና የሕግ ምርምር እና ስልጠና ኢንስቲትዩት የስራ ኃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን በቀረበው የዳሰሳ ጥናቱ ውጤት ላይ ሰፊ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የዳሰሳ ጥናት አቅራቢ ባለሙያዎቹ በሰጡት አስተያየት በተሳታፊዎች የቀረቡ ገንቢ አስተያየቶችን የዳሰሳ ጥናቱን ውጤት ለማዳበር በግብአትነት እንደሚጠቅሙባቸው ገልጸዋል፡፡ የፌደራል ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት Previous Article የዳኞችን ዕውቀት እና ክሕሎት በማጎልበት የዳኝነት አገልግሎት አሠጣጥን ጥራት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው Next Article የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባላት የትውውቅና የቃለ መሐላ መርሐ-ግብር ተካሔደ Print 1401