Friday, July 4, 2025 / Categories: News የፌደራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት አዋጅ ማሻሻያ እና የምስጋና መርሃ ግብር ተካሄደ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የፌደራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በጋራ በመሆን የፌዴራል የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 188/92 እንዲሻሻል የጥናት ሰነድ እና የአዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ አዘጋጅ ቡድን ላደረጉት የስራ ትጋትና አስተዋጽኦ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም የምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡ በኢትዬጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ስራስኪያጅ ሀጂ ከማል ሀሩን በመድረኩ ላይ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት እንደ ሙስሊም ማህበረሰብ እየተሰሩ ካሉ የለዉጥ ስራዎች ዉስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስደዉን የሸሪዓ ፍርድ ቤት ጉዳይ በሶስቱም ተቋማት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱ የረቂቅ አዋጁ ዝግጅት እንዲጠናቀቅ ረድቷል ብለዋል፡፡ በተዘጋጀዉ ረቂቅ የሸሪዓ ፍርድ ቤት አዋጅ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ እና የጥናት ሰነድ አዘጋጅ ቡድን ሰብሳቢ ክቡር ዳኛ መሀመድ አህመድ በበኩላቸዉ በፍርድ ቤቱ የሚታዩ የህግ መዕቀፍ፣ የሰዉ ሃይል አስተዳደር እና ሌሎች ተቋማዊ ችግሮችን ጨምሮ በጥናቱ የተለዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በረቂቅ አዋጁ የተደረጉ ማሻሻያዎች ተገቢ መሆናቸዉን ጠቅሰዉ ረቂቅ አዋጁ የአማርኛ ቅጂ በእንግሊዝኛ ትርጉም የተዘጋጀለት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በፌዴራል ሸሪያ ፍርድ ቤት ዉስጥ ያሉ ችግሮች በመፈተሽና መፍትሄ በመስጠት ሂደት ዉስጥ ኮሚቴዉ ያካሄደዉ ጥናት እንዲሁም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የፌደራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ባደረጉት ቅኝት የሸርዓ ፍ/ቤቱን የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እና የዳኞችንና ሰራተኞችን ቅሬታ ከመፍታት ባለፈ የህግ ማሻሻያ የሚጠይቅ መሆኑን በመለየት የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች አዋጅ እንዲሻሻል የተሰራ መሆኑን ጠቅሰዉ ተዘጋጅቶ በዛሬዉ እለት የቀረበዉ ረቂቅ አዋጅ የተሻለ አገልግሎት ሊያሰጥ የሚያስችል፣ ብዙ ጥያቄዎችን የሚመልስ እና ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል ሰነድ እንዲዘጋጅ ሆኗል ብለዋል፡፡ የረቂቅ ዝግጅት ስራዉ እንዲሳካ የሰሩት የኮሚቴ አባላት እና አስፈላጊዉን ድጋፍ በማድረግ የሰሩትን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ያደረጉት አስተዋፅኦ አመስግነዋል፡፡ በቀጣይም የተጀመሩትን መልካም ስራዎች በማስቀጠል የፍርድ ቤቱን የስራ ሂደት በመፈተሽ ተቋማዊ አቅሙን በመገንባት የተሻለ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ለማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ብዙ ስራ እንደሚጠበቅ ክቡር ፕሬዝደንት አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ክቡር ዶ/ር ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሚያደርገው ቀና ትብብርና ለተሰራዉ ትልቅ ስራ በራሳቸዉና በተቋማቸዉ ስም አመስግነው ለረጅም ዓመታት በፍርድ ቤታችን ትኩረት ያልተሰጣቸዉ ጉዳዮች በአጭር ጊዜ ዉስጥ ችግር ፈቺ በሆነ መንገድ እንዲህ መዘጋጀቱ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ የማይረሳ ታሪክ ይሆናል በማለት ምስጋናቸዉን ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም ለኢትዬጵያ እስልምና ጉዳዬች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዝደንት እና ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት በኮሚቴዉ ሰብሳቢ የተዘጋጀዉ ረቂቅ አዋጅ ርክክብ የተደረገ ሲሆን ለአዘጋጅ ኮሚቴ አባላት እና ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ላበረከቱት መልካም ስራ የምስጋና ስጦታ ተበርክቷል፡፡ Previous Article በወንጀል ነክ ድርጊት ዉስጥ ገብተዉ ከተገኙ ህጻናት እንዲሁም በሴቶች እና ህጻናት ችሎት ለሚሰሩ የፌዴራል ዳኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ Next Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር ዉይይት አደረገ Print 914