Monday, August 25, 2025 / Categories: News የፌደራል እና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ውዝፍ መዛግብትን ለማጥራት የሚያግዝ የመግባቢያ ስምምነት ከጀስቲስ ፎር ኦል-ፕሪዝን ፌሎውሽፕ ኢትዮጵያ ጋር ተፈራረሙ ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው በሚቆዩበት የክረምት ጊዜ ውዝፍ መዛግብት ማጥራትን ለመደገፍ የሚያግዝ የመግባቢያ ስምምነት (MOU) የፌደራል እና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎውሽፕ ኢትዮጵያ ከተሰኘ አገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር ነሐሴ 17 ቀን 2017 ዓ.ም ተፈራረሙ፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት በፍርድ ቤቶቹ በኩል የፌደራልና ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚደንቶች እና የፕሬዝደንቶች ተወካዮች ሲሆኑ በጀስቲስ ፎር ኦል-ፕሪዝን ፌሎውሽፕ ኢትዮጵያ በኩል ደግሞ የድርጅቱ ፕሬዚደንት ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ ናቸው፡፡ በስምምነቱ መሠረት በጎ አድራጎት ድርጅቱ ፍርድ ቤቶቹ በከፊል ዝግ ሆነው በሚቆዩበት የክረምት ጊዜ ውዝፍ መዛግብትን ለማጥራት ለሚከናውነው ሥራ ለፌደራልና ለክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን ፍርድ ቤቶቹ ደግሞ ውዝፍ መዛግብትን በማጥራት ለሕብረተሰቡ የተፋጠነ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊውን ጥረት የሚያደርጉ ይሆናል፡፡ በፊርማ ሥነሥርዓቱ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ባደረጉት ንግግር የፌደራል እና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ከጀስቲስ ፎር ኦል-ፕሪዝን ፌሎውሽፕ ኢትዮጵያ ጋር የፈረሙት መግባቢያ ስምምነት ፍርድ ቤቶችን በብዙ መልክ እንደሚያግዝና ከዚህ ውስጥም ፍርድ ቤቶች ያለባቸውን የመዝገብ ጫና ለመቀነስ በተደረሰው ስምምነት መሠረት በዳኞች በሚከናወነው ሥራ ብዙ የሕብረተሰብ ክፍልን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንና በዚህም የተገልጋዮችን እርካታ እንደሚጨምር ገልጸው ድርጅቱ ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡ ተገልጋዩ ሕብረተሰብ በፍርድ ቤቶች ላይ አመኔታ የሚኖረው ጉዳዮች በወቅቱ እልባት ሲያገኙ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የድርጅቱ ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ እስካሁን ላደረጉው ድጋፍ አመስግነው ድጋፉ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎውሽፕ ኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር በዚህ ዓመት ድርጅታቸው ከፍርድ ቤቶች ጋር ውጤታማ ሥራ የሰራበት እንደነበር አስታውሰው ለነበረው የጋራ ትብብር ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ ላይ የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎውሽፕ ኢትዮጵያ ሲኒየር አድቫይዘር ዶ/ር ውብሸት ሽፈራው ድርጅታቸው ከፌደራል እና ከክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ጋር በትብብር ሲያከናውናቸው ስለቆዩ ሥራዎች ሲያብራሩ ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው በሚቆዩበት የክረምት ወራት የተከናወኑ ሥራዎችን በተመለከተ ባለፉት 18 ዓመታት ለ274,812 ውዝፍ መዛግብት እልባት በመስጠት ዜጎች የተፋጠነ ፍትሕ እንዲያገኙ በማድረግ በመደበኛው አሰራር ውሳኔ ለማግኘት በሚጠይቀው ተጨማሪ ጊዜ ምክንያት በማረሚያ ቤት ሊቆዩ የሚችሉበትን ጊዜ ማሳጠር እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡ በፊርማ ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት የፌደራልና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚደንቶች እና ተወካዮቻቸው ከጀስቲስ ፎር ኦል-ፕሪዝን ፌሎውሽፕ ኢትዮጵያ ጋር በሌሎች የትብብር መስኮች የጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ በመድረስ የጋራ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ለተጨማሪ ውይይት የሚያቀርብ አምስት አባላት ያሉት የቴክኒክ ኮሚቴም መርጠዋል፡፡ Previous Article ሰባት (7) ዳኞች በተሰየሙበት ችሎት የተሰጡ አስገዳጅ የሰበር ውሳኔዎች ልዩ ዕትም ቁጥር 01 ለህትመት በቅቷል Next Article የተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ወጣ Print 405