Monday, February 9, 2026 / Categories: News የፌደራል ከፍተኛ እና መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የ2018 በጀት ዓመት የመንፈቅ አመት አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ ተካሄደ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት 2018 በጀት ዓመት የመንፈቅ አመት አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ በቀን 27/2018 ዓ.ም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፣ የሶስቱም ፍርድ ቤቶች አመራሮችና የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የመንፈቅ አመት ስራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ በቀረቡት ሪፖርቶች ፍርድ ቤቶቹ ቀልጣፋ ፣ተደራሽ ፣ግልፀኝነትን የተላበሰ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት ያከናወኗቸው ዝርዝር ተግባራትን በመንፈቅ አመቱ ከተያዙ ግቦች አንፃር አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሰረት በአብዛኛው ተግባራት በተለይም ከዳኝነት መዛግብት አፈፃፀም አኳያ በዕቅድ ከተቀመጠው በላይ የተሰራ መሆኑ የተገለጹ ሲሆን በአፈፃፀም ሪፖርቱ ዙሪያም በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው በየፍድ ቤቶቹ የማኔጅመንት አባላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በግምገማ መድረኩ፤ ከፍርድ ቤቶቹ የሪፖርት አቀራረብ አንፃር መሻሻሎች እንዳሉ ተገልጾ ይሁንና በአፈፃፀም የተገኙ ውጤቶች በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ለውጥ አንፃር መቃኘት እንዳለባቸው ተመላክቷል፡፡ በዚህም መሰረት የዳኝነት አገልግሎት ጥራትን በተመለከተ ከአለም አቀፍ የዳኝነት ጥራት ስታንዳርድ መለኪያ አንፃር ያለንበትን ደረጃ በመመዘን ትኩረት ተደርጎ መስራት እንደሚገባ፣ ቅልጥፍናን ለማሳደግ የዳኞችና የመዛግብት ጥመርታን ማመጣጠን እንዲሁም የቅልጥፍና ስታንዳርዶችን በድጋሚ በመፈተሽ ማስተካከያዎችን ማድረግ እንደሚገባ፣ የግልጽ ችሎት አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች ቢታዩበትም አሁንም ክትትል እንደሚያስፈልግና ማስተካከያዎች ሊደረጉ እንደሚገባ፣ በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ከተገልጋዮች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ከመፍታት አኳያ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ አሰራሮችና አደረጃጀቶችን ማጠናከር እንደሚገባ፣ ዲጂታል የዳኝነት አገልግሎቶችን አተገባበር ማጠናከር እንደሚገባ አጽዕኖት ተሰጥቶ ውይይት የተደረገባቸው ጉዳዮች ናቸዉ፡፡ በተጨማሪም የፍርድ ቤቶቹ የስድስት ወር የስራ አፈፃፀም በጋራ ማኔጅመንት መገምገሙ የዳኝነት አገልግሎቱ በሶስቱም ፌዴራል ፍርድ ቤቶች ወጥነት ባለውና በተናበበ መልኩ እንዲሰጥ የሚኖረው ሚና ከፍ ያለ መሆኑ ተጠቅሶ በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ግብዓቶችና ግብረ መልሶች የተገኙበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ይህንኑ መሠረት በማድረግም በሶስቱም ፍርድ ቤቶች ባሉ የስራ ክፍሎች መካከል የአፈጻጸም ክትትልና ድጋፎችን በማጠናከር የአገልግሎት አሰጣጥ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ Previous Article የፌዴራል መንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አዋጅ 1333/2016፣ መመሪያዎች እና ኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ አጻጸም (e-GP) ስርዓት ክህሎት ላይ ስልጠና ተሰጠ Next Article የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንቶችን እና የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመት አፀደቀ Print 323