የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ወንጀል ችሎት ምድብ የሬጅስትራር አንድ መስኮት አገልግሎት ተመረቀ
/ Categories: News

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ወንጀል ችሎት ምድብ የሬጅስትራር አንድ መስኮት አገልግሎት ተመረቀ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ወንጀል ችሎት ምድብ የሬጅስትራር አንድ መስኮት አገልግሎት ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት በክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት እና በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት በክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ ተመርቆ በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

በመርሐ-ግብሩ መክፈቻ ላይ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ ጥሪ ለተደረገለቸው እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ደግሞ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ፍርድ ቤቶች ከሚሰጡት የዳኝነት አገልግሎት ባሻገር አገልግሎቱን የሚሰጡበትን ቦታ ለተገልጋዮች እንዲሁም ለፍርድ ቤቱ ማህበረሰብ ምቹና ዘመናዊ በማድረግ የተቀላጠፈ እና የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ2017 በጀት ዓመት የተሰሩ ሥራዎች ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርቱም የዳኝነት አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ ከማድረግ አኳያ፣ ግልጽ ችሎትን ከማጠናከር አኳያ፣ ከፍርድ ጥራት፣ ከተደራሽነት፣ ከህንጻ እድሳት ጋር በተያያዘ የተሰሩ ስራዎች እንዲሁም የመዛግብት አፈጻጸምን የተመለከተ ዝርዝር ገለጻ አቅርበዋል፡፡ የቴክኖሎጂ ለውጦች በዘመናዊ ዳኝነት አገልግሎት ላይ ያለውን ሚና የሚገልጽ አጭር ጽሁፍም በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ አህመድ ኢሳ ቀርቧል፡፡

በሌላ በኩል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና በፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት መካከል የመረጃ ልውውጥ ለማድረግና በትብብር ለመስራት የሁለትዮሽ የስምምነት ፊርማ ተደርጓል፡፡

በሁለቱ ተቋማት መካከል የሁለትዮሽ ስምምነቱን የፈረሙት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኩል የፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ ሲሆኑ በፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በኩል ደግሞ የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዘና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀሚድ ኬኒሶ ናቸው፡፡

በመጨረሻም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ወንጀል ችሎት ምድብ የሬጅስትራር አንድ መስኮት አገልግሎት እውን እንዲሆን ንቁ ተሳትፎ ላደረጉ አካላት በፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንት በክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ አማካኝነት የምስጋና የምስክር ወረቀት፣የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስራ አመራር አባል ሆነው ለተሾሙት ለረጅም አመታት በዳኝነትና አመራርነት ሲያገለግሉ ለቆዩት ለቀድሞ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ተኽሊት ይመሰል የክብር አሸኛኘት ተደርጓል፡፡

Previous Article የተዘዋዋሪ እና ቋሚ ምድብ ችሎቶች ክትትል እና ግምገማን ዓላማ ያደረገ ጉብኝት ተካሔደ
Next Article በተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 ላይ ለፌደራልና ለክልል የፍትሕ ተቋማት ተሳታፊዎች ሲሰጥ የቆየው የአሰልጣኞች ሥልጠና ተጠናቀቀ
Print
1151