የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት እና ውይይት አደረጉ
/ Categories: News

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት እና ውይይት አደረጉ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች በቀን 16/04/2018 ዓ.ም፤ በ17/04/2018 ዓ.ም እና 20/04/2018 ዓ.ም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት እና ውይይት አድርገዋል፡፡

በቆይታቸውም የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የተዘረጉ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች እና የለሙ የተለያዩ መተግበሪያዎች ምልከታ ያደረጉ ሲሆን ከፍርድ ቤቱ አመራሮች እና ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የጉብኝቱ ዓላማ ዳኞች እየለሙ ላሉ የቴክኖሎጂ ስራዎች ዋነኛ ባለቤት እና ፈፃሚ በመሆናቸው ለትግበራው ምዕራፍ ስኬታማነት የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠርና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል መሆኑን ጠቅሰው እነዚህ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች እና መተግበሪያዎች የፍርድ ቤቶችን አሰራር ከማቀላጠፍና የተገልጋዮችን እንግልት ከመቀነስ ባለፈ የዳኞችን የስራ ጫና በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ እገዛ ያላቸው መሆኑን በማንሳት በቀጣይ በሚኖረው የትግበራ ምዕራፍ ዳኞች በከፍተኛ ተነሳሽነት እና የኃላፊነት ስሜት ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

አክለውም በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር የስራ ጫናን ከመቀነስና ቅልጥፍናን ከማምጣት ባሻገር ክቡር የሆነውን የዳኝነት ሙያ ሊተካ የሚችል ባለመሆኑ ቴክኖሎጂውን ከመተግበር ጎን ለጎን ሰው ተኮር አገልግሎት አሰጣጥን ባህል ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ክቡራን ዳኞቹም ባደረጉት ምልከታ እየተሰሩ ላሉ የቴክኖሎጂ ሪፎርሞች ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ ቴክኖሎጂዎችን በተመለከተ ሀሳብ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን በማንሳት ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ጉብኝቱ በጣም ጠቃሚና በትግበራ ወቅት በቀላሉ ወደ ስራ ለመግባት የሚያግዝ በመሆኑ መሰል ጉብኝቶች፤ ውይይቶች እና ስልጠናዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

Previous Article ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስርዓት የውጭ አማካሪ ምክር ቤት አባል የእውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር ተካሄደ
Next Article የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት አደረጉ
Print
411