Tuesday, April 29, 2025 / Categories: News የፌደራል የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አብይ ኮሚቴ የውይይት መድረክ ተካሄደ የፌደራል ፍትህ ተቋማት አመራሮች የተገኙበት የፌደራል የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አብይ ኮሚቴ የውይይት መድረክ በቀን 21/08/2017 ዓ.ም ተካሂዷል። የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓት ወንጀል ከመከላከል ጀምሮ የወንጀል ምርመራ፣ የወንጀል ክስና ክርክር፣ የፍርድ ቤት የዳኝነት ስርዓትና የህግ ታራሚዎችን የማረም ስራዎችን አጣምሮ የተቋማት የተናጠል እና የጋራ ሃላፊነቶችን አቅፎ የያዘ ስራ ሲሆን አብይ ኮሚቴው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽንን ያካተተ ነው፡፡ አደረጃጀቱና የአሰራር ስርዓቱ በመርህ ላይ የተመሰረተ፣ የየተቋማቱን ነጻነት ባከበረ መልኩ እንዲሆን ለማድረግ እንዲሁም የህዝብ አመኔታ ያለው እንዲሆን ለማድረግ በየተቋማቱ ካለው የለውጥ ስራ ጋር ተናባቢ እንዲሆን ለማድረግ የፌደራል የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ቅንጅታዊ አሰራር እና አደረጃጀት ቻርተር ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱ ይታወሳል፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ውስጥ በአሰራር ረገድ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመወያየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማመላከት የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን በማጠናከር ችግሮችን በየደረጃው በመፍታት ተጨባጭ ለውጦች እንዲመጡ የማድረግ፤የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ በአሰራር ረገድ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በጋራ የመቅረፍ ስራዎች በአብይ ኮሚቴው እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የጥምር ኮሚቴና የክፍለ ከተማ ኮሚቴዎችም አማካኝነት ተጠናክረው ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በመድረኩም የፌደራል ወንጀል ፍትህ አስተዳደር አብይ ኮሚቴ የ2018 በጀት አመት ዕቅድ የቀረበ ሲሆን እቅዱ የፌደራል የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ቅንጅታዊ አሰራርና አደረጃጀት ቻርተር ላይ የተገለጹትን የቅንጅት ዓላማዎች መሰረት በማድረግ በየደረጃው በተደራጁ ኮሚቴዎች የሚፈጸም መሪ እቅድ በማዘጋጀት እና የእቅድ አፈጻጸም ክትትል ግምገማ ስርዓት መዘርጋት የሚያስችል እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ መሪ ዕቅዱ የፌደራል የወንጀል ፍትህ አስተዳደርን ለማሻሻል የተለዩ ግቦችን ያካተተ ሲሆን ለአብነትም ቅንጅታዊ አሰራርን፣ ተቋማዊ እና ሙያዊ ነጻነትን ማጠናከር፣ የወንጀል ፍትህ አሰጣጥና አሰራርን ማሻሻል፣ በወንጀል ፍትህ ሂደት የህብረተሰብ ተሳትፎ ማሻሻል፣ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አካላት የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሻሻል፣ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አካላት አመራር እና ሙያተኞችን አቅም እና ስነ ምግባር ማሻሻል የሚሉት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እቅዱን የአብይ ኮሚቴው ቴክኒካል ንዑስ ኮሚቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ ውበት ጌታቸው ያቀረቡ ሲሆን ረቂቅ ሰነዱ ከቀረበ በኋላ የኮሚቴው ጠንካራ ጎኖች፣ የሚስተዋሉ ክፍተቶች፣ መልካም አጋጣሚዎች፣ ተግዳሮቶች፣ ግቦች፣ ዝርዝር ተግባራትና ፈጻሚዎችን ከግዜ ሰሌዳ ጋር የያዘ የድርጊት መርሃ ግብር ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም ከመድረኩ የተሰጡ ግብአቶችና አስተያየቶችን በማካተት እቅዱ የሚጸድቅበትን እንዲሁም በተቀሩት የበጀት ዓመቱ የስራ ጊዜያት በተለይም በክፍለ ከተማ ኮሚቴ አባላት ሊከናወኑ ስለሚገባቸው ተግባራት አቅጣጫ በማስቀመጥ የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽንና ስትራቴጅያዊ አጋርነት ዳይሬክቶሬት Previous Article በስዊድን የልምድ ልውውጥ ያደረጉ የፌደራል ዳኞች ከሶስቱም ፍርድ ቤት ለተውጣጡ ዳኞች ልምዳቸውን አካፈሉ Next Article ለፌደራል ፍርድ ቤቶች መካከለኛ አመራሮች እና ሰራተኞች ሲሰጥ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተጠናቀቀ Print 753