Monday, October 14, 2024 / Categories: News የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተጠናቀቀ በቀን 02/02/17 ዓ.ም በጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት የኢትዮጵያ ብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በመተባበር በተለያዩ ርዕሶች ማለትም የፍ/ቤት ዲጂታላይዜሽን ስራዎች፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና የቴክኖሎጂ መተግበሪያዎች ላይ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም፣ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር(INSA)፣ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ተቋማት በተገኙ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተጠናቋል፡፡ በመድረኩ መክፈቻ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያን ከሌሎች አገራት እኩል ለማራመድ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በርካታ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልጸው በፍርድ ቤቶችም የዳኝነት አገልግሎት አስጣጥን ቅልጥፍና ለማሻሻል፣ ዉጤታማነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ተደራሽነትን ለማሳደግ ቴክኖሎጂ መጠቀም ተመራጭ ብቻ ሳይሆን አስገዳጅ እየሆነ የመጣ በመሆኑ ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች በዲጂታላይዜሽንላይ እየተሰሩ ስላሉ ስራዎች ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀዉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው ጠቃሚ ግብዓት ይሆናል ብለዋል፡፡ በፌደራል ፍርድ ቤቶች እየተተገበሩ እና እየለሙ ያሉ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ የቅልጥፍናና የተደራሽነት ችግሮችን እንደሚቀርፉ አውስተው የፍርድ ቤት አሰራርን ለማዘመን ከበርካታ አጋር ተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንት አስተዳደር እና የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ አርአያስላሴ በበኩላቸው ለዜጎች የሚሰጡ አገልግሎቶች በሚገባቸው ልክ እየዘመኑ እንዲሄዱ ብዙ ስራዎች ይጠበቁብናል ያሉ ሲሆን የፍትህ ዘርፉንም በዲጂታል አቅም ማጎልበት ያለዉ ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመድረኩ የፍርድ ቤቶችን አሰራር ዲጂታላይዝ ከማድረግ አኳያ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ስላለው አስተዋጽኦ፣ የፍርድ ቤቶች ዲጂታል የለውጥ ስራዎች ያሉበት ደረጃ፣ ፍርድ ቤቶችን በዋይድ ኤሪያ ኔትወርክ ማስተሳሰር ስራ እንዲሁም ኤሌክትሮኒክስ ሪከርድ ማኔጅመንትና ICMS ላይ ሰፊ ገለጻና ውይይት ተደርጓል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ባደረጉት ንግግር በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚነሱትን የቅልጥፍና፣የጥራት፣ የተገማችነት እንዲሁም የተደራሽነት ጥያቄዎች ቴክኖሎጂን በመጠቀም እና ህጉን መሰረት አድርጎ በመስራት መመለስ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በቴክኖሎጂ አማካኝነት አሰራሮች እየተለወጡ በመምጣታቸዉ በዚሁ ልክ ዳኞችም ሆነ ሌሎች የፍርድ ቤቱ ማህበረሰብ ራስን ዝግጁ በማድረግ ህዝብና አገርን ለማገልገል ዝግጁ መሆን ተገቢ ነዉ ብለዋል ። ፕሬዝደንቱ አክለውም ፍርድ ቤት የሚለካው አንድም በፍጥነት ሌላም በጥራት በመሆኑ ይህ ካልተሳካ ፍትህን ማስፈን፣ የህዝብ እርካታን ማምጣት አይቻልም ብለዋል፡፡ ዳኞችና የፍ/ቤት ማህበረሰብ በታሪክ አጋጣሚ ያገኙትን ሃላፊነት በመጠቀም የኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች በተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኙ የራሳቸውን አሻራ እንዲያኖሩም አደራ ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ባለፈዉ ዓመት የነበሩ መልካም አፈጻጸሞችን በማስቀጠል በዚህ ዓመት የተሻለ ለማስመዝገብ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡ Previous Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች የ2017 ዓ.ም መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት በይፋ ተጀምሯል Next Article የቻይና ናሽናል የዳኞች ኮሌጅ ልዑካን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት አደረጉ Print 236