Tuesday, December 3, 2024 / Categories: News የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በአምስት የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የውይይትና ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሂዷል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች የሥልጠና ፍላጎት ዳሰሳ ጥናት፣የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሥልጠና መመሪያ፣የእግድ አሰጣት እና አተገባበር ላይ፣በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍትሕ መዘግየት ምክንያቶች እና ማነቆዎች በሚል በተዘጋጀ ሞጁል ላይ እንዲሁም የወሲባዊ ጥቃት ወንጀሎችን በተፋጠነ እና ተጎጅ ተኮር በሆነ መንገድ ለመዳኘት የሚያግዝ ማኑዋል ላይ ለሁለት ቀናት የቆየ የውይይትና ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አመራሮች፣ ከሶስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተዉጣጡ ዳኞች፣ ከህግ እና ፍትህ ኢኒስቲትዩት እና ከዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት የተወከሉ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆኑ የመጀመሪያውን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች የሥልጠና ፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ሰነድ በማዘጋጀት የተሳተፉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ክብርት ዳኛ እትመት አሰፋ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ክቡር ዳኛ አንቢኮ ጃርሳ፣ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ ክቡር ዳኛ ደረጀ ይታገሱ እና ዶ/ር ታዬ ንጉሴ ናቸው፡፡ ጥናቱ የዳኞችን እውቀት እና ክህሎት እንዲሁም ስነ ምግባር በማሳደግ ውጤታማ የዳኝነት አሰጣጥን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የስልጠና ፍላጎት ዳሰሳ ጥናት መሆኑን አንስተዋል፡፡ ሁለተኛው ሰነድ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሥልጠና መመሪያ ሲሆን መመሪያዉን በማዘጋጀት የተሳተፉት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ተክሊት ይመስል፣ የፌዴራል የህግ እና ፍትህ ኢኒስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ዘካሪያስ ኤርኮላ እና ደ/ር ዉብሸት ሽፈራው ናቸዉ፡፡ ረቂቅ መመሪያዉን ያቀረቡት ክቡር አቶ ተክሊት ይመስል የመመሪያዉ ዋና አላማ የዳኞች ሥልጠና ወጥ እና ሁሉን አቀፍ በሆነ ሥርዓት እንዲመራ ለማስቻል፣ በዳኝነት አገልግሎት ሥራ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በዳሰሳ ጥናት በመለየትና በሥልጠና ሊፈቱ የሚገባቸውን ችግሮች እና የፍርድ ቤቶችን አጠቃላይ ዓላማ በሥልጠና ለ መደገፍ፤ ከዳኝነት ሥራ ጋር በቀጥታ ተጓዳኝ የሆኑ የአስተዳደር ሠራተኞችን አቅም በሥልጠና በማጎልበት ሥነ-ምግባራቸውንና የሥራ አፈጻጸማቸውን በማሻሻል የተሻለ የሥራ እርካታ ያለውና የተረጋጋ ሠራተኛ እንዲኖር ለማገዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሌላው ሰነድ የእግድ አሰጣጥ እና አተገባበር ላይ የተዘጋጀው ሞጁል ሲሆን ሰነዱን በማዘጋጀት የተሳተፉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ክቡር ዳኛ ተሾመ ሽፈራው እና ክቡር ዳኛ ዶ/ር ተፈሪ ገብሩ ናቸዉ። ይህ ሞጁል ከፍርድ በፊት የሚሰጥ የንብረት ማስከበር እና የጊዜያዊ እግድ ትዕዛዝ አሰጣጥ ስርዓት በህጉ እና ተቀባይነት ካላቸዉ መርሆዎች አንፃር የሚዳሰስ፣ ከህጉ አተገባበር ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ዳኞች በሚገባ እንዲገነዘቡ የሚያደርግ፣ ጊዜያዊ የእግድ ትዕዛዝ መሰጠቱ የሚያስከትለውን በጎም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ተረድተዉ ስለጉዳዩ የሚደነግገዉን የፍትሐብሔር ስነ-ስርዓት ህጉን ድንጋጌዎች መሰረት በማድረግ ተገቢዉን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑ ተብራርቷል፡፡ አራተኛዉ ሰነድ ደግሞ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍትሕ መዘግየት ምክንያቶች እና ማነቆዎች በሚል ሞጁል ሲሆን ጥናቱን በማጥናት የተሳተፉት ክቡር ዳኛ ሀብታሙ እርቅይሁን፣ ክቡር ዳኛ አበበ ሰለሞን እና ክቡር ዳኛ እንዳለ ታደሰ ሲሆኑ የዳሰሳ ጥናቱ ዋና ዓላማም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በፍትህ አሰጣጥ ጉዳዮች መዘግየት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን እና ክፍተቶችን ለይቶ የመፍትሔ ሃሳብ ማቅረብ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በመጨረሻም የወሲባዊ ጥቃት ወንጀሎችን በተፋጠነ እና ተጎጂ ተኮር በሆነ መንገድ ለመዳኘት የሚያግዝ ማኑዋል የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመራሮች፣ከሶስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተዉጣጡ ዳኞች፣ ከትግራይ፣ ከአማራ እና ከአፋር ክልል ፍርድ ቤቶች የተዉጣጡ ዳኞች በተገኙበት ቀርቧል፡፡ ሰነዱን ያዘጋጁት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ክቡር ዳኛ መላኩ ካሳዬ እና ክብርት ዳኛ ሠናይት አድነው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ክቡር ዳኛ ጌትነት መዲና፣ በመቀሌ የኑዘርሲቲ የህግ መምህር ዶ/ር ኃይሌ አብርሃ፣ በባህዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር እና በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፕሬዝዳንቱ ልዩ አማካሪ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ወርቁ ያዜ ናቸዉ፡፡ ማኑዋሉን ማዘጋጀት ያስፈለገው በዋነኛነት በጦርነት እና በግጭት ወቅት የወሲባዊ ጥቃት ወንጀሎች ከተፈጸሙ ጉዳዩን በተፋጠነ እና ተጎጂ ተኮር በሆነ መልኩ መዳኘት ለማስቻል መሆኑ ተገልጿል፡፡ በቀረቡት ሁሉም ሰነዶች ላይ ከተሳታፊዎች ገንቢ አስተያያትና በአቅራቢዎችም ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ Previous Article በሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በተዘጋጀ ረቂቅ የጥናት ሰነድ ላይ ውይይት ተካሄደ Next Article በተባበሩት መንግስታት የህጻናት መብቶች ኮሚቴ አማካኝነት እየተዘጋጀ ባለው General Comment 27 on Access to Justice for children ላይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት ተካሄደ Print 859