የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህንጻ ግንባታ ማስጀመሪያ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ
/ Categories: News

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህንጻ ግንባታ ማስጀመሪያ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህንጻ ግንባታ ማስጀመሪያ የፊርማ ሥነ ሥርዓት በቀን 19/05/2017 ዓ.ም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት፣የከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዝደንት፣የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትርና ሚኒስትር ዴኤታ፣ የዳኞች ተወካዮች እና የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የፌደራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት እና በይርጋለም ኮንስትራክሽን መካከል ነው፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የህንፃ ግንባታው የዜጎችን በግልፅ ችሎት የመዳኘት ህገመንግስታዊ መብት ለማስከበር የሚረዳ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ ቀደም በቂ የማስቻያ ቦታዎች ባለመኖራቸዉ ሲነሱ ለነበሩ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት፣ የፍትህ አገልግሎትን በአንድ ማዕከል ተደራሽ ለማድረግ፣ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን በማካተት የተቋቋመበትን አላማ ለማሳካት፣ በአጠቃላይ የዜጎችን ህገመንግስታዊ መብት ለማረጋገጥ የሚረዳ ነው ብለዋል።

ለተገልጋዮች ቀልጣፋና ዉጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ግንባታው በሚፈልገዉ ፍጥነት እና ጥራት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ግዙፍና በሀገር ውስጥ ኮንትራክተር የሚተገበር መሆኑን ገልፀው፤ በሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ዕድገት ማሳያና ማስቀጠያ ከመሆኑም ባሻገር የፍትህ ስርዓቱ ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ይህንን ታሳቢ በማድረግ በተሻለ ብቃት በመፈፅም በታሰበለት ግዜ ሊጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ይዞታው የሚገኘው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክ/ከተማ በአዲሱ ወረዳ 9 ሲሆን የቦታው ስፋት 14742.99 ካሬ ሜትር፣ህንጻው የሚያርፍበት ቦታ ስፋት 5,926 ካ.ሜ ሆኖ ግንባታው 3 ህንፃዎችን አካቶ የያዘ ነው። በ4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የሚገነባው ይህ ህንጻ እስከ መስከረም 2019 ዓ.ም ድረስ የሚጠናቀቅ መሆኑ ተገልጿል፡፡

Previous Article በኢፋይሊንግ፣ ኢሊቲጌሽን እና ኤሌክትሮኒክ ሪከርድ አመራር አፈጻጸም ረቂቅ መመሪያ ላይ የውይይት መድረክ ተካሄደ
Next Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስርዓት የውጭ አማካሪ ምክር ቤት ዓመታዊ የውይይት መድረክ ተካሄደ
Print
957