Monday, August 4, 2025 / Categories: News የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2017 ዓ.ም አመታዊ የስራ አፈጻጸም የግምገማና የውይይት መድረክ ተካሄደ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2017 ዓ.ም አመታዊ የስራ አፈጻጸም የግምገማና የውይይት መድረክ ሀምሌ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ መድረኩን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በበጀት አመቱ የተመዘገበው ውጤት ከእቅድ አንጻር ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት መሆኑን ጠቅሰው በተለይም ከመዝገብ አፈጻጸም፣ ከበጀት አጠቃቀም፣ ከኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም እና አተገባበር እንዲሁም ከተገልጋይ እርካታን ከማሳደግ አንጻር የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበበት ዓመት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ከውሳኔዎች ጥራትና ውዝፍ መዛግብትን ከማጥራት አንጻር የሚታዩ ክፍተቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የሚደረገው ግምገማና የውይይት መድረክ ካለፈው አመት አፈጻጸም በመነሳት የተመዘገቡ መልካም አፈጻጸሞችን በማስቀጠል እንዲሁም የታዩ ክፍተቶች ላይ በመምከር በቀጣይ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ የዳኞችና የአስተዳደር ሰራተኞች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በተነሳሽነት ስሜት ለተሻለ አፈጻጸም መትጋት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ደረጃ በበጀት አመቱ ከመዝገብ አፈጻጸም አኳያ ለ189,905 መዛግብት ዕልባት ለመስጠት በዕቅድ ተይዞ ለ190,347 መዛግብት ዕልባት የተሰጠ ሲሆን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለ22,690 መዛግብት እልባት ለመስጠት ታቅዶ ለ18,951 መዛግብት ዕልባት በመስጠት ካለፈው አመት የላቀ አፈጻጸም ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በማጠቃለያ ንግግራቸው ለተገኘው የመልካም አፈጻጸም ውጤት ምስጋናቸውን አቅርበው ከዳኝነት አገልግሎት አንጻር ታቅደው ያልተከናወኑ እንዲሁም ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየባቸው ጉዳዮች በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራባቸው ገልጸዋል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ በበኩላቸው ዳኞች በከፍተኛ የስራ ጫና ውስጥ በመሆን መልካም ውጤት እንዲመዘገብ ያደረጉት አስተዋጽኦ የሚመሰገን መሆኑን አንስተው እንደ ክፍተት የታዩ ጉድለቶችን ደግሞ በመፈተሸ የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ አጠቃላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2017 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም ፣ የሬጅስትራር ጽ/ቤት፣ የአውሮፓ ህብረት የወንጀል ፍትህ ስርአት ማሻሻያ ፕሮጀክት፣ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር፣የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች አሁናዊ የአፈጻጸም ደረጃ ሪፖርቶች እንዲሁም የዳኝነት ኢንስፔክሽን ጥናት የቀረቡ ሲሆን አጠቃላይ በቀረቡ ሪፖርቶች ላይም ፍርድ ቤቱ በበጀት አመቱ ሊያሳካ ካሰባቸው ግቦች አንጻር የተመዘገቡ መልካም አፈጻጸሞች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ ቁልፍ የትኩረት መስኮች በማመላከት ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ Previous Article የሰበር ሰርዓትን ማጠናከር ለዳኝነት ሪፎርም በሚል የቀረበ ጽሁፍ ላይ ውይይት ተደረገ Next Article በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ የተመራ ልዑክ ቡድን "የተቀናጀ የጉዳዮች ማኔጅመንት ሲስተም እና የኤሌክትሮኒክ ሪከርድ ማኔጅመንት"(Integrated Case Management System and Electronic Record Management) ላይ ኬንያ በመገኘት የልምድ ልው Print 773