የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች የእርስ በእርስ የዉይይት መድረክ በይፋ ተከፈተ
/ Categories: News

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች የእርስ በእርስ የዉይይት መድረክ በይፋ ተከፈተ

ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች የእርስ በርስ የዉይይት መድረክ ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ ተጀምሯል

ዉይይቱ ለአንድ ዓመት የታቀደና በየወሩ አንድ ጊዜ የሚደረግ ሲሆን ፍርድ ቤት በህዝብ ዘንድ አመኔታን ያተረፈ እንዲሆን እና ወጥነት ያለዉ ዉሳኔ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ለመወሰን የሚያስችል ወሳኝ ጉዳዬች ላይ ትኩረት አድርጎ ዳኞች እርስ በእርስ እንዲወያዩ የሚያስችል ነው

ዉይይቱን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በዚህ ዉይይት ልዩነት የፈጠሩ ጉዳዮችን እንዲሁም በስራ ላይ ካለዉ ህግ ያፈነገጡ አሰራሮችን ወደ አንድ መስመር በማምጣት የሚሰጡ ዉሳኔዎችን ተገማች ለማድረግ መድረኩ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል

በእለቱ በተደረገዉ ዉይይትም ሆነ በቀጣይ በሚደረጉ ተመሳሳይ የዳኞች የእርስ በእርስ ዉይይቶች ዳኞች በጋራ የሚወስዷቸዉን ሀሳቦች በስራ ላይ በማዋል ወጥ የሆነ አሰራር በፍርድ ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያግዝ ክቡር ፕሬዝደንቱ አክለዋል

በመድረኩ ‹‹በፌዴራል ፍረድ ቤቶች መዝገብን ወደ ስር ፍርድ ቤት የመመለስ ህግና አሰራር ››በሚል ርዕስ የተዘጋጀና ከዋናዉ ዳሰሳ ጥናት የተወሰደ ጥናታዊ ጽሁፍ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምርምርና ህግ ጉዳዬች ዳይሬክቶሬት የህግ ጥናት ምርምር ባለሙያ በሆኑት አቶ ካሚል እድሉ ቀርቦ ሰፊ ዉይይት ተደርጓል

ዳኞች በዉይይቱ ከመሳተፍ ባለፈ ሃሳቦችን በማቅረብና በማመንጨት የዉሳኔዎችን ወጥነትና ተገማችነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ርዕሰ ጉዳችን በማቅረብ የጋራ ዉይይት እንዲደረግባቸዉ ጥሪ ቀርቧል

Previous Article “ወደ ፍርድ ቤት የሚመጡ ህጻናት ልጆቻችን ናቸው ፍላጎታቸውን እና መብቶቻቸውን ልናከብርላቸው ይገባል”
Next Article የፌዴራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1233/13 እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/13ን ለማሻሻል የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተዘጋጀ
Print
490