Monday, December 1, 2025 / Categories: News የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍርድ አፈጻጸም ጽ/ቤት ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ የንብረት አገማመት መምሪያዎች/ማኑዋል ላይ ውይይት ተካሄደ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍርድ አፈጻጸም ጽ/ቤት ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ የንብረት አገማመት መምሪያዎች/ማኑዋሎች ላይ ከቀን 20/03/2018 ዓ.ም-21/03/2018 ዓ.ም ለ2 ቀናት የቆየ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ ከፈደራል ፍርድ ቤቶች የተውጣጡ ዳኞችና የስራ ሃላፊዎች፣ የፍትህ ሚኒስቴር የንብረት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በውይይት መድረኩ የተንቀሳቃሽ ንብረቶች መገመቻ አገልግሎት አሰጣጥ ማንዋል እና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች መገመቻ እና አገልግሎት አሰጣጥ ማንዋልን የተመለከቱ ገለጻዎች የቀረቡ ሲሆን ገለጻውን ተከትሎም ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ማኑዋሎቹ የተዘጋጁት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ አፈጻጸም ጽ/ቤት ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይ ለሚስተዋሉ የአደረጃጀት፣ የአሰራር እና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እልባት ለመስጠት ነው፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ድሪባ ፈዬራ በመድረኩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ አፈጻጸም ጽ/ቤትን ለማጠናከርና ውጤታማነቱንም ለማሳደግ በፍርድ ቤቱ የስትራቴጂ ሰነድ ላይ የተካተቱ በርካታ የሪፎርም ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው ከእነዚህም መካከል ጽ/ቤቱ ካለበት የስራ ፍሰትና ሃላፊነትን ከግምት ያስገባ መዋቅራዊ አደረጃጀት መዘርጋቱ፣ አስተዳደራዊ እርምጃዎች በተለያዩ ግዜያቶች መወሰዳቸው፣ የጽ/ቤቱን የአሰራር ስርአት ለመዘርጋት መመሪያ መውጣቱ እንዲሁም መመሪያውን ተከትሎም መምሪያዎች/ማኑዋሎች መውጣቸው ከብዙ በጥቂቱ ናቸው ብለዋል ፡፡ አክለውም ለውይይት የቀረቡት መምሪያዎች ፍርድ ከማስፈጸም ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጥናት በመለየት በጥልቀት የታየ በመሆኑ ከመድረኩ ከተነሱ ሀሳቦችና በቀጣይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በሚኖር መድረክ ከሚገኙ ተጨማሪ ግብአቶች ጋር የዳበረ ሰነድ ሆኖ እንደሚጸድቅ ገልጸዋል፡፡ Previous Article የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የናሚቢያ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረሙ Next Article የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP Ethiopia) ጋር በጋራ ስለሚሰሩባቸው ጉዳዮች ተወያዩ Print 502