Friday, January 2, 2026 / Categories: News የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት አደረጉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀን 22/04/2018 ዓ.ም በመገኘት ጉብኝት አድርገዋል፡፡ አፋር ሲደርሱም በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ከፍተኛ የመንግሥት ተቋማት ሃላፊዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ በቆይታቸውም የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፍርድ ቤቶችን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የሚያግዝ የአይሲቲ ፕሮግራም ማስጀመሪያ መርሀ ግብርን ከአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከክቡር ሀጂ አወል አርባ ጋር በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍርድ ቤት የቪድዮ ኮንፍረንስና ኢፋይሊንግ ማዕከል አገልግሎትንም እንዲሁ አስጀምረዋል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ቴክኖሎጂ በሂደት እየተስፋፋ የሚሄድ እንደመሆኑ ፍርድ ቤቶችን ለማዘመን ባለ አቅም ክልሉ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባና ከጠቅላይ ፍርድ ቤትና በዞን ፍርድ ቤቶች ጀምረው በማስፋፋት ማዳረስ እንደሚገባ ለዚህም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማንኛውንም አይነት ቴክኒካል ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም የዳኝነት አገልግሎቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ከክልሉ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ፍርድ ቤት መጥተው በተጨባጭ የሚያጋጥመውን ችግር እየለዩ የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ክቡር ሀጂ አወል አርባ በበኩላቸው በክልሉ የሚተገበሩ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ከፌደራል ጋር እየተናበቡ መሄድ እንዳለባቸውና በፌደራል ፍርድ ቤቶች እየተተገበረ ያለውንም ክልሎች የየራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ዉስጥ በማስገባት ወደ ራሳቸው ወስደው እንዲጠቀሙ ማድረግ ውጤታማነቱን እንደሚያረጋግጥ ገልጸው ክልሉ በዚህ ረገድ አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ክቡር ፕሬዝደንት ከፍርድ ቤቶች በተጨማሪ ከወንጀል ነክ ጉዳዮች ውጭ በርከታ ጉዳዮች የሚፈቱበት የአፋር ባህላዊ የሙግት መፍቻ ስርአትን የጎበኙ ሲሆን ይህ ባህል ለመደበኛ ፍርድ ቤት አጋዥ ከመሆኑም በላይ የማህበረሰቡን በሰላም አብሮ የመኖር ባህል እንደሚያዳብር አንስተዋል፡፡ Previous Article የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት እና ውይይት አደረጉ Next Article በፍትህ ሥርዓት ውስጥ የሚያልፉ ህጻናትን መብት በማስጠበቅ ሂደት የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎችን ሚና ለማጠናከር የሚያግዝ ወርክሾፕ ተካሄደ Print 267