Thursday, February 27, 2025 / Categories: News የፌደራል ፍርድ ቤቶችን የለውጥ ሥራ ተፈጻሚ ለማድረግ የፍርድ ቤቶችን የሰው ኃይል አቅም መገንባት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለጸ በፌደራል ፍርድ ቤቶች የተጀመረውን የለውጥ ሥራ ተፈጻሚ ለማድረግ የፍርድ ቤቶችን የሰው ኃይል አቅም መገንባት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ ገለጹ፡፡ ክብርት ምክትል ፕሬዝደንት ይህን የገለጹት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባዘጋጀውና ከሶስቱም የፌደራል ፍርድ ቤቶች ለተውጣጡ 110 ሠራተኞች ከየካቲት 20-22 ቀን 2017 ዓ.ም በተዘጋጀው የሶስት ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መክፈቻ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤቶች በጀመሩት የለውጥ ሥራ የተከናወኑ እና በመሠራት ላይ ያሉ ማሻሻያዎች እንደሚገኙ የጠቆሙት ም/ፕሬዚደንት ከእነዚህ መካከል የሕግ ማሻሻያዎች፣ የቴክኖሎጂ ሥራዎች እና የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ሥራዎችን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው እነዚህ ማሻሻያዎች የሚተገበሩት በሰው ኃይል በመሆኑ የሰው ኃይል ግንባታ ትኩረት ከተሰጣቸው የለውጥ ሥራዎች መካከል የሚመደብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ፍርድ ቤቶቹ ተግባራዊ ያደረጉትን ለውጥ መሠረት በማድረግ የሚሰጡ አገልግሎቶች ቅልጥፍና፣ ጥራት እና ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆን ከፍርድ ቤቶች የሰው ኃይል ምን እንደሚጠበቅ በቂ ግንዛቤ መያዝ፣ ለአንድ ዓላማ በጋራ መስራት እንዲሁም በቁርጠኝነት መፈጸም ከእያንዳንዱ ሠራተኛ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ለሶስት ቀናት በሚቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሰው ሀብት ሥራ አመራር ደንብ እና መመሪያዎች፣ ተቋማዊ ለውጥ፣ የሥራ ባህል እና ሥነምግባር፤ አዲሱ የህዝብ አገልግሎት አቀራረብ ስልት ለተሻለ ተቋማዊ አፈጻጸም እንዲሁም የዲጂታላይዜሽን ጉዞ በፌደራል ፍርድ ቤቶች በሚሉ ርዕሶች ላይ ሥልጠና የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ስልጠናው በተከታታይ 7 ዙሮች የሚሰጥ ሲሆን በክልል ከተሞች የሚገኙ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ሠራተኞችን ባካተተ ሁኔታ አሁን በሥልጠናው ላልታቀፉ ሌሎች ባለሙያዎችና የስራ ሃላፊዎችን ባሳተፈ መልኩ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ Previous Article የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ልዑክ ቡድን በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት አደረጉ Next Article በከባድና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ የተዘጋጀ ሥልጠና ለፌዴራል እና ክልል ፍርድ ቤቶች ዳኞች ተሰጠ Print 941