የፌደራል ፍርድ ቤቶችን የዳኝነት ነጻነት፣ ገለልተኝነት እና ተጠያቂነትን ለማጠናከር የተወሰዱ እርምጃዎች
/ Categories: News

የፌደራል ፍርድ ቤቶችን የዳኝነት ነጻነት፣ ገለልተኝነት እና ተጠያቂነትን ለማጠናከር የተወሰዱ እርምጃዎች

የካቲት 6 ቀን 2014 ዓ.ም «የፌደራል ፍርድ ቤቶች አሁናዊ ሁኔታ» ዓመታዊ ጉባኤ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ባቀረቡት ሪፖርት በ2013-2014 በጀት ዓመት አጋማሽ በፍርድ ቤቱ የሪፎርም ሥራዎች ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራትን ዳስሰዋል፡፡ ክብርት ፕሬዚደንትዋ ዛሬም ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ባይባልም የፌደራል ፍርድ ቤቶችን የዳኝነት ነጻነት፣ ገለልተኝነት እና ተጠያቂነትን ለማጠናከር የተለያዩ እርምጃዎች የተወሰዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህ የገለልተኝነት እና የነጻነት ጉዳይ ዳኞች ከውጭም ሆነ ከውስጥ ጣልቃ ገብነት ተጽዕኖ ሳይደርስባቸው ሕግን ብቻ ተከትለው ውሳኔ እንዲሰጡ አስፈላጊ ሁኔታዎችን ማመቻቸትን ይጠይቅ ነበር ብለዋል፡፡ የዳኝነት ነጻነት የዳኞች ነጻነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ፍ/ቤቱም እንደተቋም ለማንኛውም የፖለቲካም ሆነ ማህበራዊ ጫናዎች የተጋለጠ እንዳይሆን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እና እርምጃዎችንም መውሰድ ይጠይቅ እንደነበር ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ እንደተከናወኑ ከጠቀሷቸው ተግባራት መካከል፡-

• ይህን ግብ ለማሳካት የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ባቀፈ መልኩ የፌዴራል ፍ/ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 ተሻሽሎ መውጣቱ፣

• የፍ/ቤቱን ዋና የፖሊሲ አቅጣጫ ለመወሰን አቅም ያለው፣ ተገቢ በሆነ ደረጃ የዳኞች ተወካዮች የሚሳተፉበት፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤን ያቋቋመው የተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1233/2013 መውጣቱ፣

• እነዚህን ህጎች ተግባራዊ ለማድረግ በአዋጆች የተመለከቱ 22 ያክል ደንቦች እና መመሪያዎችን አስመልክቶ ሰፊ ጥናቶች፣ የኮሚቴ ስብሰባዎች እና የአመራር ስብሰባዎች በማድረግ እንዲጸድቁ መደረጉ ወይም ተረቀው በመጽደቅ ሂደት ላይ መሆናቸው፣

• በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ይጸድቃል ተብሎ የሚጠብቀው የፌዴራል ፍ/ቤቶች አስተዳደር ሰራተኞች ደንብ፣ የፌዴራል ዳኞች የስነ-ምግባር እና የዲሲፒሊን ክስ ስነስርዓት ደንብ፣ የጉዳዮችን መጨናነቅ ስርዓት ለማስያዝ እንደሚያግዝ የታመነበት የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ፣ የፍ/ቤት መር አስማሚነት እና ሌሎችም መመሪያዎች የዳኝነት ነጻነት፣ ተጠያቂነት፣ ፈጣን አገልግሎት እና ውጤታማነትን ለማምጣት ቁልፍ ሚና ያላቸው መሆኑ፣

• የዳኝነት ነጻነትን ከማስከበር አኳያ የፍ/ቤቶችን በጀት በቀጥታ በሕ/ተወካዮች ምክር ቤት ማስወሰን መቻሉ፣ የፍ/ቤቱ በጀት በም/ቤቱ መቅረቡ እና መጽደቁ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን የፍ/ቤቱን ፍላጎት ለማስረዳት እና በተከታታይ ዓመታት የፍ/ቤቱ በጀት ከ 40% በላይ እንዲያድግ እድል የፈጠረ መሆኑ፣

• የዳኞች ነጻነትን ለማስጠበቅ አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችለው ሌላው እርምጃ ለረጅም ዓመታት ሲጠየቅ የነበረና ሳይመለስ የቆየው የዳኞች የደመወዝና ሌሎች ጥያቄዎችን የማስወሰን ጉዳይ እልባት ማግኘቱ፣

• የዳኞች መኖሪያ ቤት ተጠናቆ በከፊል ዳኞች የገቡ ቢሆንም የህንጻው የመጨረሻ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ህንጻውን ለማስገንባት ኃላፊነት የወሰደው የመንግስት ተቋም አንዳንድ ችግሮች ስላጋጠሙት በታሰበበት ጊዜ መጠናቀቅ ባይችልም የመጨረሻውን ስራ ከዳር ለማድረስ እየተጋ የሚገኝ መሆኑና በአመራሩ እና በዳኞች አስተዳደር ጉባኤም ስራው ፍጻሜ እንዲያገኝ የሚቻለው ጥረት እየተደረገ መሆኑ በዚህ ዙሪያ ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በጉባዔው ላይ ያቀረቡት ሙሉ ሪፖርት ከዚህ በታች ባለው መስፈንጠሪያ ያገኑታል፡፡

https://www.fsc.gov.et/.../%e1%8b%a8%e1%8d%8c%e1%8b%b4%e1...

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article «የፌደራል ፍርድ ቤቶች አሁናዊ ሁኔታ እና የወደፊት ዕይታ» በሚል ርዕስ የተዘጋጀ መድረክ ተካሔደ
Next Article ፍርድ ቤቱ ለአራት ክልሎች ጠቅላይ ፍ/ቤቶች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
Print
1669