የፌደራል ፍርድ ቤቶች መደበኛ የችሎት ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሄደ
/ Categories: News

የፌደራል ፍርድ ቤቶች መደበኛ የችሎት ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሄደ

የፌደራል ፍርድ ቤቶች መደበኛ የችሎት ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ፣የፌደራል ፍርድ ቤት አመራሮች፣ክቡራን ዳኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተካሂደል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በፕሮግራሙ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር በ2017 ዓ.ም በርካታ ስራዎች የተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው በ2018 ዓመት በጀት ዓመት ባለፈው ዓመት የተገኙ መልካም ውጤቶችን ማስፋት፣ የቀሩትን ሟሟላት፣ አዳዲስ አሰራሮችን ማስተዋወቅ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ አንስተው ዓመቱ የ5 ዓመት ስትራቴጂ ዘመን ማብቂያ እና የ3 ዓመት የለውጥ ፍኖተ ካርታ ማጠናቂቂያ በመሆኑ ያለፈውን ውጤት በመገምገም ቀጣይ ምዕራፍ የሚጀመርበትና የመጪውን ዘመን ፍኖተ ካርታ የሚቀየስበት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የፍርድ ቤት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ ታግዞ መስጠት ጋር በተያያዘ የተጀመሩት ስራዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ወደ ስራ የሚገቡበት በመሆኑም ቀጣዩ ትኩረት ትግበራውን ማፍጠን ነው ብለዋል፡፡

አክለውም አዲሱ የስራ ዘመን በተሻለ የስራ መንፈስና ተነሳሽነት፣ በውጤታማነትና ትጋት በመስራት በውጤቱም ፍትህ ሰፍኖ የህብረተሰቡ እርካታ የሚረጋገጥበት እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው የፍርድ ቤቶችን አገልግሎቶችን ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በገለልተኝነትና በነጻነት እንዲያከናውኑ የህግ አሰራር ማሻሻያዎች፣ ምቹ የስራ ከባቢን ለመፍጠር የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች ማስፋፋት እንዲሁም የፍርድ ቤት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመግለጽ የዜጎችን አመኔታ ያተረፈ የፍትህ ስርዓት መገንባት የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከቀን 03/2018 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩ ሲሆን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍትሐብሄር ይግባኝ ሰሚ ችሎት አድራሻም ቀድሞ ከነበረበት ከአብረሆት ቤተ መጸሕፍት 100 ሜትር ዝቅ ብሎ ፍርድ ቤቱ አዲስ እያስገነባ ባለው ህንጻ ውስጥ የሚጀምር መሆኑን በድጋሚ እናሳውቃለን፡፡

Previous Article በሶማሌ ክልል መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አሊ ባሩድ የተመራ ልዑክ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት የልምድ ልውውጥ አደረገ
Next Article ለፌደራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ
Print
396