የፌደራል ፍርድ ቤቶች ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በፓናል ውይይት አከበሩ
/ Categories: News

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በፓናል ውይይት አከበሩ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ111ኛ ጊዜ፣ በአገራችን ደግሞ ለ46ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) የፌደራል ፍርድ ቤቶች የካቲት 29 ቀን 2014 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል በፓናል ውይይት አከበሩ፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የፓናል ውይይቱን በንግግር ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር የሴቶች የሲቪልም ሆነ የፖለቲካ መብት እና ተሳትፎ ከኢኮኖሚ መብት ጋር ተያያዥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ማሳያው የግል ገቢ የሌላት ሴት ከሚበድላት ባል ጋር ለመኖር እንደምትገደድና አማራጭ የሥራ ዕድል የሌላት ሴትም የመጥፎ አለቃን እብሪትና ትንኮሳ ችላ ለመኖር የምትገደድ መሆንዋ ትስስሩን እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡

ክብርት ፕሬዚደንቷ በንግግራቸው የጠበቆች የሙያ ማሕበር በቅርቡ መቋቋሙ በሀገራችን በፍትሕ ዘርፍ ለተጀመረው የማሻሻያ ሥራ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸው፣ቀደም ሲል የነበሩ የሕግ ባለሙያዎች ለዚህ እውን መሆን ትኩረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው ዛሬ ይህ ዕድል መገኘቱን እንደታሪካዊ ስኬት በመመልከት ዕድሉን በአግባቡ እንድንጠቀምበት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ አሸነፈች አበበ በፌደራል ፍ/ቤቶች ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ፣ በዳኝነቱም ሆነ በአስተዳደር ዘርፍ ከሥርዓተ ጾታ አንጻር የተከናወኑ ተግባራትን አቅርበዋል፡፡

በፌደራል ፍ/ቤቶች የተከናወነውን ሲገልጹም በአመራር ደረጃ 35 ከመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውንና ይህም ቁጥር ቀደም ሲል ከነበረው መጠን አንጻር ሲታይ ትልቅ እመርታ ማሳየቱን አስገንዝበዋል፡፡ ይህም ቁጥር በየፍ/ቤቶቹ ደረጃ ሲታይ በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት 23 በመቶ ያህሉ ሴት ዳኞች ሲሆኑ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት እና በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በቅደም ተከተል 36 እና 37 በመቶ ያህሉ ሴት ዳኞች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የሴቶች ውክልናን በረዳት ዳኝነት እና በሬጅስትራርነት የስራ መደቦች ላይ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራቱንና በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት እና በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በሬጅስትራር የስራ መደብ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ከጾታ አንጻር ተመጣጣኝ እንደሆነ ጠቅሰው ረዳት ዳኞችን በተመለከተም ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ሴቶች በሰብሳቢ ዳኝነትና በተጠሪ ዳኝነት የስራ መደቦች ላይ ከመመደብ አንጻር በሶስቱም ፍ/ቤቶች ቀደም ሲል ከነበረው የተሻለ አፈጻጸም የሚታይ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ከችሎት ምደባ ጋር በተያያዘም የሚወጡ መመሪያዎች ሴቶችን ያሳተፉ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በአስተዳደር ዘርፉም በሶስቱም ፍ/ቤቶች ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሴት አስተዳደር ሠራተኞች እንደሆኑ ጠቅሰው ባለፉት ሶስት ዓመታት በፌደራል ፍ/ቤቶች በሹመት፣ በቅጥር እና በዕድገት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡

ወደፍ/ቤቶች የሚመጡ ሴት ባለጉዳዮችን መብት ከማስከበር አኳያም በተደረጉ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች መሠረት ለሴቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት አቅም የሌላቸው በጠበቃ እንዲታገዙ የጠበቆች ጽ/ቤትን ከማደራጀት ጀምሮ የተፋጠነ ፍትሕ እና የቀደምት አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የጠበቆች ማሕበር ፕሬዚደንት ወ/ሮ ስንዱ አለሙ በዳኝነት እና በጥብቅና አገልግሎታቸው ካካበቱት ዕውቀት ልምዳቸውን በመድረኩ ለታደሙ ዳኞች አካፍለዋል፡፡

በሌላ በኩል የእናት ባንክ የማርኬቲንግ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ አክሊል ግርማ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ባንኩ ባለፉት ዓመታት ያደረገውን አስተዋጽኦ አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ከታሳታፊዎች ለቀረቡ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ከመድረኩ አወያዮች መልስ ተሰጥቶበታል፡፡

የፓናል ውይይቱ በፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት እና በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሴቶችና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት እንዲሁም በፌደራል ፍ/ቤቶች ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን በመድረኩ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት እና የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ፕሬዚደንቶች፣ የፍ/ቤቶቹ አመራሮች፣ ዳኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማ የሚሆነው ከባለድርሻ አካላት እና ከሕብረተሰቡ አስፈላጊው ትብብር እና ድጋፍ ሲሠጠው መሆኑን ገለጹ
Next Article የፍ/ቤቱ ዳኞች በጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር እና በመዛግብት አፈጻጸም ዙሪያ አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸው ተገለጸ
Print
78

Documents to download