የፌደራል ፍርድ ቤቶች የፍርድ አፈጻጸም ጽ/ቤት የአሰራር ስርዓት መመሪያ ላይ የቫሊዴሽን ወርክሾፕ ተካሄደ
/ Categories: News

የፌደራል ፍርድ ቤቶች የፍርድ አፈጻጸም ጽ/ቤት የአሰራር ስርዓት መመሪያ ላይ የቫሊዴሽን ወርክሾፕ ተካሄደ

የፌደራል ፍርድ ቤቶች የፍርድ አፈጻጸም ጽ/ቤት የአሰራር ስርዓት መመሪያ ላይ የቫሊዴሽን ወርክሾፕ በቀን 24/12/2017 ዓ.ም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት፣ የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዝደንት፣ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች እና የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

የመመሪያው አላማ የፍርድ ቤቶችን የፍትሐብሄር የአፈጻጸም ትእዛዞችን ፍትሐዊ፣ ግልጽና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስፈጸም፣ የፍርድ ቤት ትእዛዞች በአግባቡ መከበራቸውን ማረጋገጥ፣የተከራካሪ ወገኖች መብት ማክበርና ማስከበር እንዲሁም የፍርድ ቤት ትዕዛዞችን ተፈጻሚነት በማረጋገጥ ህብረተሰቡ በፍርድ ቤት ላይ ያለውን አመኔታ ከፍ ለማድረግ ነው፡፡

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ በፍርድ አፈጻጸም ጽ/ቤት የሚሰሩ የፍርድ ማስፈጸም አሰራር ስርዓት ላይ ግልጽነት ያለው እና ወጥ የሆነ የአሰራር ሰርዓት በመዘርጋትና ይህ የአሰራር ስርዓት የህግ መሰረት እንዲኖረው በማድረግ ፍርድ የማስፈጸም አቅምን ማጠናከር እና የተገልጋይ እርካታን ማሳደግ አስፈላጊነትን መነሻ በማድረግ መመሪያው የተዘጋጀ መሆኑን አንስተዋል፡፡

አክለውም በጽ/ቤቱ የሚከናወኑ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ውሳኔ ማስፈጸም ሂደት በርካታ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ እና ዝርዝር ቴክኒካዊ እውቀቶችን የሚጠይቅ እንደመሆኑ መጠን ስርዓት ባለው መንገድ ካልተመራ ለብልሹ አሰራር መጋለጡና ተገልጋይን ለእንግልት መዳረጉ አይቀርም ብለዋል፡፡

የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ዳንኤል ገዛኽኝ በበኩላቸው መመሪያው ከብዙ ጥረት በኋላ ለቫሊዴሽን በመቅረቡ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ፀድቆ ወደ ስራ ሲገባም በፍርድ አፈጻጸም የስራ ሂደት ውስጥ ሲያጋጥሙ የነበሩ የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት የአገልግሎት አሰጣጡን እንደሚያቀላጥፍ ብሎም የተገልጋዮችን እርካታ እንደሚጨምር ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የመመሪያውን ይዘትና አላማን በተመለከተ የፍርድ አፈጻጸም ጽ/ቤት ሃላፊ ዳኛ እንዳለ ታደሰ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ገለጻውን ተከትሎ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

መድረኩ የተዘጋጀው በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ትብብር ነው፡፡

Previous Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕንጻ ግንባታ ያለበት ደረጃ ተገመገመ
Next Article ዓመታዊ የስራ ዕቅድና አፈጻጸም እንዲሁም የሰራተኞች ፕሮግራም ተካሄደ
Print
339