የፌደራል ፍርድ ቤቶች የ2016 በጀት አመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግምገማ ተደረገ
/ Categories: News

የፌደራል ፍርድ ቤቶች የ2016 በጀት አመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግምገማ ተደረገ

የፌደራል ፍርድ ቤቶች የ2016 በጀት አመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ በቀን 28/09/2016 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቀርቦ ተገምግሟል

ሪፖርቱን ያቀረቡት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በፌደራል ፍርድ ቤቶች ባለፉት 9 ወራት የተከናወኑ ስራዎችን ከሪፎርም እና የመዛግብት አፈጻጸም እንዲሁም አገልግሎት አሳጣጥ ጋር በተገናኘ የተመዘገቡ አፈጻጸሞችን አቅርበዋል

የመዛግብት አፈጻጸምን በተመለከተ በ2016 በጀት ዓመት በፌደራል ፍርድ ቤቶች በ9 ወራት ውስጥ ለ143,455 መዛግብት ዕልባት ተሰጥቷል። ይህ አፈጻጸም ከየፍርድ ቤቶች አንጻር ሲታይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት 12,853 ፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤት 19,973 መዛግብት፣ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለ110,629 ዕልባት ተሰጥቷል

በቀረበው ሪፖርት ላይ የዳኝነት አገልግሎቱን ግልጽ፣ተደራሽ፣በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው ከማድረግ አኳያ፣የዳኝነት ነጻነትና ገለልተኛነት አተገባበር ከማሻሻል፣ ውዝፍ መዛግብትን ከማጥራት አንጻር ውጤታማ ሥራ መከናወኑ እንዲሁም ከዳኝነት አገልግሎት ጥራት ጋር በተያያዘ የተከናወነው ሥራ ፍርድ ቤቶች በተገልጋዩ ሕብረተሰብ እምነት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አፈጻጸም ላይ የበጀት፣ የሰው ሀይል እጥረትና የዳኞችና የመዛግብት ቁጥር አለመጣጣም እንደ ተግዳሮት የተነሱ ሲሆን በእነዚህ የሰው ሀይልና የበጀት ውስንነት መስራት መቻሉም ተጠቁሟል

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ኢሳ ቦሩ በበኩላቸው ፍርድ ቤቶቹ ከአገልግሎት አንጻር ከመዛግብት አፈጻጸም ጀምሮ በግልጽ ችሎት የማስቻልና ለዲሲፕሊን ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱ ፣ የህግ ማሻሻያና የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ላይ ወደ ትግበራ መገባቱ እንዲሁም አገልግሎቶችን ለማዘመን ከኢመደአ (ኢትዮጵያ መረብ ደህንነት አስተዳደር)፣ ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እንዲሁም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመሆን የተሰሩ ስራዎች አበረታች መሆቸውን ጠቅሰው አገልግሎት አሰጣጥን ከማሻሻልና የህዝብ አመኔታን ከማትረፍ አንጻር ጅምር ስራዎች ተጠናቀው ወደ ትግበራ ሊገቡ እንደሚገባ፣ የመዛግብት ፍሰትን ከማስተካከል አንጻር በስታንዳርድ የመስራትና የተደረሰበትን የጥራናት ቅልጥፍና ደረጃ መለካት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እጸገነት መንግስቱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ከማድረግ አኳያ የተጀመሩ የቴክኖሎጂ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ፣ የመዝገብ ኦዲትና የኢንፔክሽን የአሰራር ስርአት በፍርድ ቤቶቹ መዘርጋት እንዲሁም ከክልል ፍርድ ቤቶች ጋር እየተሰሩ ያሉ የመቀናጀት ስራዎች መልካም ጅምሮች መሆናቸውን ጠቅሰው የሕዝብ ተሳትፎንና ኮሙኒኬሽን ሥራዎችን ማጠናከር እንዲሁም ምቹ የስራ አካባቢን ማረጋገጥ አስፈላጊነት በመጥቀስ እንደ አጠቃላይ በፌደራል ፍርድ ቤቶች እየተመዘገቡ ያሉ መልካም ለዉጦች በማጠናከር ማስቀጠል እንደሚገባም ተጠቁመዋል

Previous Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፍኖተ ካርታ የ9 ወር እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተደረገ
Next Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዋይድ ኤርያ ኔትወርክ ዝርጋታ የመስክ ጉብኝት ተደረገ
Print
4975