የፌደራል ፍርድ ቤቶች የ2017 ዓ.ም መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት በይፋ ተጀምሯል
/ Categories: News

የፌደራል ፍርድ ቤቶች የ2017 ዓ.ም መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት በይፋ ተጀምሯል

በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/13 በተደነገገው መሠረት በየዓመቱ ከነሐሴ 1 እስከ መስከረም 30 ድረስ ለሁለት ወራት በከፊል ዝግ ሆነው እንደቆዩ የሚታወስ ሲሆን መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ከዛሬ ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሯል።

በመክፈቻ ሥነሥርዓቱ ላይ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚደንቶች እና ም/ፕሬዚደንቶች፣ የፌዴራል ፍትህ እና ህግ ኢንስቲቲዩት አመራሮች፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኞች፣ የፌደራል ከፍተኛ እና መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ተጠሪ ዳኞች፣ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በመክፈቻ ሥነሥርዓቱ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ባደረጉት ንግግር በ2016 ዓ.ም በርካታ የሪፎርም ስራዎች የተሰሩበትና ውጤታማ አፈጻጸም የታየበት፣ በተለይም የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን በማሳደግ ቅልጥፍናና ተደራሽነትን በማሻሻል ረገድ መልካም ውጤት የተመዘገበበት ዓመት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

አክለውም ውጤቱን ለማስመዝገብ ክቡራን ዳኞች፣ የስራ ኃላፊዎች፣ የፍርድ ቤት ሰራተኞች እንዲሁም ከፍርድ ቤቱ ጋር በአጋርነት ሲሰሩ የነበሩ የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ሚና የላቀ እንደነበር ጠቅሰው ለዚህም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ ከተለያዩ ሚዲያዎች ለቀረቡ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በፍ/ቤቶቹ በ2016 በጀት ዓመት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት እንዲሁም የትኩረት አቅጣጫዎችም በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት ከመዝገብ አፈጻጸም አኳያ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከቀረቡ 24,591 መዛግብት መካከል ለ16,636 መዛግብት እልባት መሰጠቱ፣ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 31,989 መዛግብት ቀርበው 24,853 መዛግብት እልባት ማግኘታቸውና በተመሳሳይም በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤቶች 155,915 መዛግብት ቀርበው 135,233 መዛግብት እልባት ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ተቋማዊ ነጻነትን የጠበቀ ገለልተኛ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ የሕግና አሰራር ማዕቀፎችን የማጠናከር፤ የፍርድ ቤት እና ሌሎች የመንግስት አካላት የእርስ በእርስ ግንኙነት መድረኮችን በማመቻቸት የቅንጅት ስራዎችን የማስፋት፤ የዳኞችን ሁለንተናዊ ደህንነት በማረጋገጥ ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ጥራት ያለውና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ የስራ ሁኔታዎች ማጎልበት ይገኙበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የዳኝነት አገልግሎት ድጋፍ የሚሰጡ ሰራተኞችን ተነሳሽነት ማሳደግ የሚያስችሉ ምቹ የስራ ሁኔታዎችን የማሻሻል፤ ተጠያቂነት በማስፈን የተገልጋዮችን ቅሬታዎችን መፍታት የሚያስችሉ በመመሪያ የተደገፉ ምዘናዎች እንዲሁም የኢንስፔክሽንና ፍርድ ስራ ምርመራዎችን የማጠናከር፤ የተከላካይ ጥብቅና፣ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት፣ የሕጻናት ፍትህ፣ የቋንቋ ትርጉም አገልግሎት፣ የተዘዋዋሪ ችሎት አገልግሎቶችን፣ እንዲሁም ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ተደራሽነት በማጠናከር አካታች የሆነ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት የፍርድ ቤቶቹ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚሆም ተጠቅሷል ፡፡

በሌላ በኩል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ በፌደራል ፍርድ ቤቶች በጅምር ላይ ያሉ የኢኮቴ ቅንጅታዊ ፕሮጀክቶችን ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲገቡ የማድረግና የዳኝነት አገልግሎቱ ለተገልጋይ ምቹ፣ ዘመናዊ እና ቀልጣፋ እንዲሆን የማድረግ ተግባራት የቀጣይ አመት የትኩረት አቅጣጫዎች ይሆናሉ፡፡

Previous Article የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ልዑክ ቡድን በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት የልምድ ልውውጥ አደረገ፡፡
Next Article የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተጠናቀቀ
Print
305