የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፍኖተ ካርታ የ9 ወር እቅድ አፈጻጸም  ግምገማ ተደረገ
/ Categories: News

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፍኖተ ካርታ የ9 ወር እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተደረገ

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፍኖተ ካርታ የ9 ወር አፈጻጸም ግምገማ በሀገራዊ የፍርድ ቤቶችና የፍትህ አካላት ትራንስፎርሜሽን የስራ አፈጻጸም የምክክር መድረክ ላይ በቀን 23/09/2016 ዓ.ም ቀርቧል::

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ የዳኝነትና የፍትህ አካላት የህግ የበላይነት የሚከበርባቸውና የህዝብ ተአማኒነት ያተረፉ እንዲሆኑ ለማስቻል ምክክር በማድረግ ጠንካራ ጎኖችን ማጎልበት፣ ጉድለቶችን መለየትና መማማር እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መለየትና በአሰራር፣ በአደረጃጀት፣ በቴክኖሎጂ፣ በአቅም ግንባታ እና በልዩ ልዩ ማዕቀፎች የፍትህ አካሉን ማጠናከር አስፋላጊ መሆኑን ገልጸዋል::

የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ፍኖተ ካርታ የ9 ወር አፈጻጸም ሪፓርት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በፌደራል ፍርድ ቤቶች ከዳኝነት ነጻነት፣ ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ከማረጋገጥ፣ ከብቃትና ከህሎት፣ ከተደራሽነት፣ ከውጤታማ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ከቅልጥፍናና ውጤታማነት፣ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት፣ ከአደረጃጀትና አሰራር እንዲሁም ከቅንጅታዊ አሰራር ጋር በተያያዘ በፌደራል ፍርድ ቤቶች የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ በርካታ ስራዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል::

በፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ነጻነትን፣ተጠያቂነት፣ ጥራትና ቀልጣፋ አግልግሎትን ለማረጋገጥ የወጡ ደንቦች፣ በሂደት ላይ ያሉ ረቂቅ የአዋጅ ማሻሻያዎች፣ ደንብና መመሪያዎችም ዳሰሳ የተደረገባቸው ሲሆን ፍርድ ቤቶቹ አፈጻጸም ላይ እያጋጠሟቸው ያሉ የበጀትና የሰው ሀይል ውስንነት፣ የህግ ማሻሻያ የሚሹ የሪፎርም ስራዎች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች እንደ ተግዳሮት ተነስተዋል፡፡

እነዚህና መሰል ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የአመራር ተገቢ ክትትል እና ቁርጠኝነት፣ በቅንጅት የመስራትና ህብረተሰቡን የማሳተፍ ስራዎች እንዲሁም አቅም በፈቀደ መጠን ተገቢው የበጀት ምደባ ማድረግ በቀጣይ ሊወሰዱ ከሚገባቸው እርምጃዎች ውስጥ እንደሆኑ በመግለጽ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚሆኑም ተጠቁሟል

በመድረኩ የፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ ካርታ እና የፍትህ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን መርሃ ግብር አተገባበርን አስመልክቶ የመስክ ምልከታ ሪፖርት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የተገመገሙ ሲሆን ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ የመፍትሄ ሀሳቦች ቀርበውም ውይይት ተደርጎባቸዋል

የዳኝነትና የፍትህ አካላት ሪፎርም አበረታች መሆናቸውንና በቀጣይ አቅም በፈቀደ መጠን የተናበቡ እንዲሆኑ በቅንጅት መሰራት እንዳለባቸው፣ የጋራ መድረኮች ላይ በጋራ በመምከር በዳኝነትና ፍትህ ስርአቱ ላይ የሚነሱ ችግሮችን መፍታትና በህዝብ የተጣለባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ስርአት ዘርግቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተነስቷል

Previous Article የፌደራል ፍትህ አካላት የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አብይ ኮሚቴ የውይይት መድረክ ተካሄደ
Next Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች የ2016 በጀት አመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግምገማ ተደረገ
Print
1342