የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚደንቶች፣ አመራሮችና ዳኞች ለክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ የእንኳን ደስ አለዎት መርሐ-ግብር አካሔዱ
/ Categories: News

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚደንቶች፣ አመራሮችና ዳኞች ለክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ የእንኳን ደስ አለዎት መርሐ-ግብር አካሔዱ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የክርክር ፍርድ ቤት የግማሽ ጊዜ ዳኛ ሆነው መሾማቸውን ምክንያት በማድረግ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚደንቶች፣ ዳኞችና የሥራ ኃላፊዎች ሕዳር 13 ቀን 2015 ዓ.ም በፍርድ ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ የእንኳን ደስ አለዎት መርሐ-ግብር አካሔዱ፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ በመርሐ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ክቡር ም/ፕሬዝዳንቱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላገኙት ሹመት በመንግሥት በኩል ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ይህ ስኬት ሌሎችንም እንደሚያነሳሳ ጠቁመው ለአገራችንም የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ካሉ በኋላ፣ ክቡር አቶ ሰለሞንን «እንኳን ደስ አለዎት»፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውንም «እንኳን ደስ አላችሁ» ብለዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ስኬቶች የሚገኙት የፍርድ ቤተቱ ዳኞችና ሠራተኞች በሠሩት ሥራ ላይ በመመስረት ነው ያሉት ክብርት ፕሬዚደንትዋ፣ ስኬት በመደጋገፍ ላይ የሚመጣ መሆኑን ጠቁመው ለአገር መሥራትም ትልቅ እርካታ አለው ብለዋል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ብርሐነመስቀል ዋጋሪ በበኩላቸው ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በፌደራል ፍርድ ቤቶች በቆዩበት ጊዜ በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር ዳኞችን የማሰልጠን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ የቆዩ መሆኑን በማስታወስ ቀጣዩ የሥራ ዘመን የተሳካ እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ አሁን ያገኙት ስኬት በአንድ በኩል እርሳቸው በግል በሰሯቸውና ባስመዘገቧቸው ውጤቶች የተገኙ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት አራት ዓመታት በፌደራል ፍርድ ቤቶች በተከናወኑ ሥራዎች የተገኙ በመሆኑ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ተሿሚዎች ውጤት ነው በማለት ደግሞ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ተስፋዬ ንዋይ አስገንዝበዋል፡፡

ም/ፕሬዝዳንቱ አክለውም ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ የሚኖራቸው ውክልና ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተሳትፎአቸው አነስተኛ ለሆኑ ሕዝቦችና አገራት ጭምር ነው ብለዋል፡፡

ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በበኩላቸው ለተዘጋጀው የእንኳን ደስ አለዎት መርሐ-ግብር ምስጋናቸውን ገልጸው በውድድሩ ብዙ ሒደቶችን አልፈው ለስኬት ለመብቃት በመንግሥት የተደረገላቸው ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በመሰል ውድድሮች ላይ መሳተፍ የአገራችንን ፍላጎት ለማሳካት ያለውን ጠቀሜታ አስረድተው በየጊዜው ሰዎችን በማብቃት በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ኃላፊነቶች ላይ ለመወዳደር ራሳቸውን ሊያዘጋጁ እንደሚገባ ለመድረኩ ተሳታፊዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፤ ለተዘጋጀላቸው መርሐ-ግብር እና ለተበረከተላቸው ስጦታም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article በፌደራል ፍርድ ቤቶች የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ እና በሶስት ወር አፈጻጸም ላይ ለቋሚ ኮሚቴ አባላት ማብራሪያ ቀረበ
Next Article ሪፖርተር ጋዜጣ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ከክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ጋር ያደረገዉን ቃለ ምልልስ ሕዳር 10 ቀን 2015 ዓ.ም በእንግሊዝኛ ቋንቋ እትሙ እንደሚከተለው አቅርቦታል
Print
1852