የፌደራል ፍትህ አካላት የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አብይ ኮሚቴ የውይይት መድረክ ተካሄደ
/ Categories: News

የፌደራል ፍትህ አካላት የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አብይ ኮሚቴ የውይይት መድረክ ተካሄደ

የፌደራል ፍትህ አካላት የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አብይ ኮሚቴ የውይይት መድረክ ግንቦት 22 ቀን 2016 ዓ.ም በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርአት ውስጥ ከአሰራርና ከህግ ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ውይይት ተካሂዷል

ፕሮግራሙን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በወንጀል ፍትህ አስተዳደር የፍትህ ተቋማት የአሠራር፣ የአደረጃጀት እንዲሁም የአመለካከት ማነቆዎች ላይ በጋራ በመወያየትና ስራዎችን በጋራ በመገምገም መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ የዳኝነትና የፍትህ አካላቱን ውጤታማ፣ ቀልጣፋ እና የህግ የበላይነትን የሰፈነበት አገልግሎት እንዲሆን በማድረግ የማህበረሰብ ፍላጎት ከማርካት በተጨማሪ የወንጀል ፍትህ ስርዓቱ በህግ የበላይነት እንዲመራና የሀገሪቱ ሰላም እና ደህንነት እንዲጠበቅ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል::

በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ ውጤታማ የሆነ የዳኝነትና የፍትህ ዘርፍ አሰራር አንዲጠናከር ማድረግ፣ ንፁሃን መብታቸው እንዳይጣስና ወንጀል ፈፃሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ፣የፍርድ ቤት ዉሳኔ እንዲከበር፣ በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እና ለብልሹ አሰራር እንዲሁም ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ አሰራሮችን ለመቅረፍ የፍትህ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራርን ጉልህ ሚና እንዳለው አክለዋል::

የዐቃቤ ህግና የፖሊስ ተቋምን በሚመለከት የሚነሱትን ችግሮችና የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ በፍትህ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ ወ/ሮ ውበት ጋሻው ፣ፍርድ ቤቶችን በሚመለከት የሚነሱትን ችግሮችና የመፍትሄ ሃሳቦች በተመለከተ ደግሞ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነትና አስተዳደር ዘርፍ ዋና አማካሪ በሆኑት በአቶ ቦጃ ታደሰ ቀርበዋል::

በቀረቡት ሰነዶችና የጋራ አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ቀጣይ አጀንዳዎችና የትኩረት አቅጣጫዎች ተለይተው ተቀምጠዋል፡፡ በቻርተሩ የተዘረጋውን አላማ በሚያረጋግጥ መልኩ ለውጥ ለማምጣት በየፍትህ ተቋማቱ እየተሰሩ ያሉ የሪፎርም እና የቴክኖሎጂ ስራዎች በተናጠል ለውጥ የሚያመጣ ስለማይሆን በጋራ በመሆን ስራዎቹ ተመጋጋቢ እንዲሆኑና ተቋማቱ እየተነባቡ እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋልም ተብሏል::

የፍትህ ተቋማት ስራዎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያተኮሩና ተናባቢ እንደመሆናቸው መጠን የጋራ እቅድ ተይዞላቸው ጥናትን መሰረት ባደረገ ሁኔታ ስራዎች በቅንጅት እንዲከናወኑ እና አሰጣጣቸውን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ተቋማቱ ተግዳሮቶቻቸው ላይ በጋራ በመምከር የመፍትሄ ሃሳቦች እንዲያቀርቡ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል::

የፌደራል የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አብይ ኮሚቴ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም የፌዴራል ወንጀል ፍትህ አስተዳደር ቅንጅታዊ አሰራር እና አደረጃጀት ለመደንገግ በወጣው ቻርተር መሰረት በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሂደት የፍትህ ተቋማት በጋራ በሆኑ ሥራዎቻቸው ላይ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የተቋቋመ መሆኑ የሚታወስ ነው::

Previous Article የፌደራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1233/13 እና የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/13 የማሻሻያ ሀሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሄደ
Next Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፍኖተ ካርታ የ9 ወር እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተደረገ
Print
438