Monday, February 9, 2026 / Categories: News የፌዴራል መንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አዋጅ 1333/2016፣ መመሪያዎች እና ኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ አጻጸም (e-GP) ስርዓት ክህሎት ላይ ስልጠና ተሰጠ ከመንግስት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አዋጅ 1333/2016፣ መመሪያዎች እና ኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ አጻጸም (e-GP) ስርዓት ክህሎት ላይ ከጥር 21 እስከ 23/2018 ዓ.ም ለሦስት ቀናት ስልጠና ተሰጥቷል ፡፡ ሥልጠናው ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የአስተዳደር ዘርፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ነሞ አዱኛ የስልጠናውን አስፈላጊነት ሲገልጹ አሁን ላይ እየተሰራባቸው ያሉት የግዥ እና ንብረት አስተዳደር አዋጅ እና መመሪያዎች ቅርብ ጊዜ የወጡ በመሆኑ በፍ/ቤቱ ያሉ እና በዘርፉ ኃላፊነት የተሰጣቸዉ አካላትም በአዲስ አደረጃጀት የስራ ስምሪት የተሰጣቸዉ በመሆኑ የግዥ እና የሚወገዱ ንብረቶች አጽዳቂ ኮሚቴ፣ የቴክኒክ ኮሚቴዎች፣ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሞያዎች በቂ ግንዛቤ ኖሯቸዉ በተቀናጀ፣ በብቃት እና በጥራት ኃላፊነታቸዉን እንዲወጡ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ አጻጸም (e-GP) ላይም የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማሻሻል እስከ ዉል አስተዳደር ያለዉ ሙሉ ሂደት በመተግበር ረገድ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ በትኩረት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ስልጠናውን የሰጡት ከመንግስት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን መስሪያ ቤት የፕሮጀክት ጽ/ቤት ሲነየር ባለሙያ ወ/ሮ ወገኔ ተገኝ እና ባለሞያ የሆኑት አቶ አላዘር ተስፋዬ ሲሆኑ ስልጠናው ያተኮረዉ ቀድሞ የነበረው የግዥ እና ንብረት አዋጅ፣ መመሪያዎች እና አሰራሮች ከአዲሶቹ ጋር ሲታይ የተሻሻሉትን ጉዳዮች እና በአተገባበር ወቅት የታዩ የአሰራርና የትርጉም ክፍተቶችን ግልጽ በማድረግ ሰልጣኞች የተሻለ ግንዛቤ በሚያገኙት መልኩ ስልጠናዉን ሰጥተዋል፡፡ ሰልጣኞች የመንግስት የግዥ ድንጋጌዎችን፣ የግዥ ዘዴዎችን፣ ዉጤታማ የግዥ አፈጻጸም ስልቶችን እና ሌሎች ነጥቦች ላይ ለሰልጣኞች ግንዛቤ አስጨብጠዋል፡፡ ስልጠናዉ በተለይም ኤሌክትሮኒክስ የግዥ ስርዓት "e-GP" አስመልክቶ የነበሩትን የአተገባበር ክፍተቶች በሚሞላ መልኩ በፍ/ቤቱ የስልጠና ማዕከል የተግባር ስልጠና ጭምር የተሰጠ ሲሆን ሰልጣኞቹም ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ስልጠናው ላይ የተሳተፉት የግዥና ንብረት አስተዳደር ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የግዥና የሚወገዱ ንብረቶች አጽዳቂ ኮሚቴ አባላት፣ የቴክኒክ ኮሚቴዎች አባላት፣ ኦዲቴሮች እና የኢኮቴ ባለሞያዎች ናቸው፡፡ Previous Article ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሬጂስራርና ችሎት አገልግሎት ክፍል ለተውጣጡ ሰራተኞች ስልጠና ተሰጠ Next Article የፌደራል ከፍተኛ እና መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የ2018 በጀት ዓመት የመንፈቅ አመት አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ ተካሄደ Print 541