Monday, March 17, 2025 / Categories: News የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት የአንድ መስኮት አገልግሎት እና የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለሚ ኩራ ምድብ ችሎት የመስክ ጉብኝት ተካሄደ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት እና በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለሚ ኩራ ምድብ ችሎት በመገኘት ጉብኝት አድርገዋል። ክቡር ፕሬዝደንቱ በእለቱ ባደረጉት ንግግር በፌደራል ፍርድ ቤቶች እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ስራዎች መጠነ ሰፊ እንደመሆናቸው በዚህ ልክ የፍርድ ቤት ተገልጋይ ማህበረሰብ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ አገልግሎት ሰጪ ሰራተኛው በየፍርድ ቤቶቹ የተዘረጉትን ዘመናዊ አሰራሮች ለመጠቀምና ለመተግበር ዝግጁነትና ፈቃደኝነትን በመላበስ በአገልጋይነት መንፈስ በሞራል ልዕልና ከፍ ብሎ የሚታይ ሰራተኛ መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ ክቡር ፕሬዝደንቱ አክለውም የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥ እና በግልጽ ችሎት የማስቻል ሁኔታ ላይ እንዲሁም የተገልጋዮችን ቅሬታ ከመፍታት አንጻር ዳኞች እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ያላቸውን ሚና በማንሳት ፍርድ ቤት በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን አመኔታ ለማሳደግ የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ በበኩላቸው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍትሐብሄር ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን ጉዳዮች እና በወንጀል ከባድ እና ውስብስብ እንዲሁም ከሀገር ኢኮኖሚ፣ ሰላም እና ጸጥታ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮችን የሚያስተናግድ ፍርድ ቤት እንደመሆኑ መጠን በዚህ ልክ ትኩረት ተሰጥቶት ለባለጉዳዮች ተደራሽና ግልጽ በሆነ መንገድ፣ አገልግሎቱን ከአንዱ ቢሮ ወደ ሌላ ቢሮ ሳይዘዋወሩ ፋይል ከመክፈት ጀምሮ እስከ ውሳኔ ድረስ በአንድ መስኮት ወጪ እና ግዜ ቆጣቢ በሆነ ሁኔታ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኮሚዩኒኬሽንና ስትራቴጅያዊ አጋርነት ዳይሬክቶሬት Previous Article የፍርድ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መልካም ስነ ምግባርን በመላበስ የተቋሙን ራዕይ ማሳካት እንደሚገባ ተገለጸ Next Article ስዊድን አገር ለተደረገው የስራ ጉብኝትና ልምምድ ልውውጥ ስኬት ላበረከቱ አካላት የምስጋና መርኀ ግብር ተካሄደ፡፡ Print 726