Monday, July 28, 2025 / Categories: News የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አርባ ምንጭ ማዕከል የህንፃ እድሳት ምርቃት መርሃግብር ተካሄደ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አርባ ምንጭ ማዕከል የህንፃ እድሳት ተደርጎ በሐምሌ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ተመርቋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጉብኝነት በማድረግ ላይ የሚገኙት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የህንፃ እድሳት ምርቃት ስነ ሥርዓቱን የጉብኝታቸው ማጠቃለያ በማድረግ በመርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን የማስቻያ ስፍራዎችን ምቹ ማድግና አካላዊ ተደራሽነትን ማረጋገጥ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አንዱ የለውጥ ግብ መሆኑን አንስተው ሌሎች የለውጥ ስራዎችንም በተለይም የ ቴክኖሎጂን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የዳኝነት ስርዓቱን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት በትጋት ሊሰራ እንደሚገባ አንስተዋል። ክቡር ፕሬዚደንቱ አክለውም ህንፃው በዘመናዊ መልክ ታድሶ ለዳኝነት አገልግሎት ዝግጁ እንዲሆን ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል:: የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ በበኩላቸው የህንፃው መታደስ የተሻለ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን እና ህንፃው አስቀድሞ ከነበረው ገፅታ አንፃር በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሳካ እድሳት መደረጉ የዳኝነት ስራውን ለማዘመን የተጀመሩ በርካታ ጥረቶች ስኬት ማስያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል መሆኑን አንስተው የታደሰውን ህንፃ ከመስጠት ጀምሮ በህንፃ እድሳቱ ወቅት ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉትን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጋሞ ዞን እና የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር አመራሮችን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤትን፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠ/ፍ/ቤት እና ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመራሮችን እንዲሁም ሌሎች በህንፃ እድሳት ስራው ላይ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል:: በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አመራሮች እና የከፍተኛ ፍ/ቤት ተጠሪ ዳኞች ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና የጋሞ ዞን እንዲሁም የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ታድመዋል :: Previous Article የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የእውቅና ሽልማት አበረከተ Next Article ለኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማሕበር ጽ/ቤት የሰበር ውሳኔዎች የድምጽ ቅጂ ተበረከተ Print 870