የፌዴራል  ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1233/13 እና የፌዴራል  ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/13ን ለማሻሻል የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተዘጋጀ
/ Categories: News

የፌዴራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1233/13 እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/13ን ለማሻሻል የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተዘጋጀ

የፌዴራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1233/13 እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/13ን ለማሻሻል የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በጀስቲስ ፎር ኦል ኘሪስን ፌሎሺፕ ትብብር በቀን 17/09/2016 ዓ.ም የሶስቱም ደረጃ ፍርድ ቤቶች አመራሮች፣ተጠሪ ዳኞች፤ ሰብሳቢ ዳኞች እና የስራ ክፍል ኃላፊዎች በተገኙበት ተደርጓል::

መድረኩን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ መድረኩ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚፈለገዉን ዉጤት ለማምጣት የሚረዱ ሃሳቦችን የህግ መሰረት እንዲኖራቸዉ ለማስቻልና አሁን በስራ ላይ ያሉ አዋጆች በአተገባበር ወቅት የታዩ ክፍተቶችን ለማረም እንዲሁም ፍርድ ቤቶች በህገ መንግስቱ ከተሰጣቸዉ ኃላፊነት አንፃር የሚፈለገዉን ለዉጥ ለማምጣት መሰረት የሚጥል የህግ ማዕቀፍ ለማበጀት ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል::

የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፎሎሺፕ ኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ በበኩላቸው የፍርድ ቤቱን ተቋማዊ እና የዳኞችን ግለሰባዊ ነፃነት ባስጠበቀ መልኩ ግልፅና ፍትሃዊ ዳኝነት ለመስጠት እነዚህ ህጎች መሻሻላቸዉ አስፈላጊ ናቸዉ ብለዋል::

የፌዴራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1233/13 ለማሻሻል አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት፣የማሻሻያ ሂደቱ፣እንዲሻሻሉ የተፈለጉት ጉዳዬች፣አዲስ እንዲጨመሩ የተነሱ እና ከማሻሻያ አዋጁ እንዲወጡ የተፈለጉ ጉዳዬችን የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ድሪባ ፌዬራ እንዲሁም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር ዳኛ አበበ ሰለሞን ያቀረቡ ሲሆን በማሻሻያዉ አዳዲስ የተካተቱ ድንጋጌዎች እና ንዑስ አንቀጾች እንዲሁም ሙሉ ለሙሉ ከአዋጁ እንዲወጡ የተደረጉ ድንጋጌዎችም ቀርበዉ በርካታ የግብኣት ሀሳቦችና አስተያየቶች ለመድረኩ ቀርበዋል

በቀረቡት ገለጻዎችና የማሻሻያ ሃሳቦች ላይ ዉይይት የተደረገ ሲሆን በግብዓትነት የቀረቡ ሃሳቦች ተወስደው በትግበራ ወቅት አላሰራ ያሉ ጉዳዬች የበለጠ ትኩረት በመስጠት ለይቶ በማዉጣት የብዙሃኑን ሃሳብ ያካተተ የተሟላ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ተጨማሪ ግብዓቶች እንዲሰጥባቸዉ ይደረጋል ተብሏል::

በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ከውጭ ባለድርሻ አካላት ጋር ማክሰኞ ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም ተጨማሪ የግብዓት ማሰባሰቢያና የውይይት መድረክ የሚኖር ይሆናል::

Previous Article የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች የእርስ በእርስ የዉይይት መድረክ በይፋ ተከፈተ
Next Article የፌደራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1233/13 እና የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/13 የማሻሻያ ሀሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሄደ
Print
470