የፌዴራል ዳኞች የጉባዔ ተወካዮቻቸውን መረጡ
/ Categories: News

የፌዴራል ዳኞች የጉባዔ ተወካዮቻቸውን መረጡ

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች በፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የሚወክሏቸውን 3 ዳኞች መረጡ፡፡

የቀድሞውን የዳኞች አስተዳድር ጉባዔ አዋጅ 684/2002ን ለማሻሻል የወጣው የፌዴራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ 1233/2013 አስራ አምስት ዓባላት ያሉት የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ያቋቋመ ሲሆን በአዋጁ እንቀጽ 6(1/ቀ) መሰረት ከሶስቱም ፌዴራል ፍርድ ቤቶች በዳኞች ጠቅላላ ስብሰባ የተመረጡ አንድ ወንድ እና ሁለት ሴት ዳኞች በድምሩ ሶስት ዳኞች አባል እንዲሆኑ ይደነግጋል፡፡

በዚሁ መሰረት የሶስቱም ፌዴራል ፍ/ቤቶች ማትም የፌዴራል ጠቅላይ፤ ከፍተኛ እና መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤቶች ዳኞች ዛሬ ሐምሌ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል ባካሄዱት ጠቅላላ ስብሰባ ተወካዮቻቸውን መርጠዋል፡፡

በምርጫው ሒደት ከእያንዳንዱ ፍርድ ቤት ሁለት ሴት እና አንድ ወንድ በአጠቃላይ ስድስት ሴት እና ሶስት ወንድ ዕጩ ተወካይ ዳኞች በጥቆማ ከተመረጡ በኋላ በጠቅላላ ስብሰባው የተገኙ ዳኞች በተናጠል በምስጢር ለእጩዎቹ ደምጽ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

ምርጫው በአስመራጭ ኮሚቴ እና በታዛቢዎች የተመራ ሲሆን ዳኛ ወ/ሮ ትንሳኤ ሸዋለም ከመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት 134 ድምጽ በማግኘት፤ ዳኛ ወ/ሮ ፀሐይ መንክር 121 ድምጽ በማግኘት እና ዳኛ አቶ በረከት ስይፉ 116 ድምጽ በማግኘት በአብላጫ ድምጽ አሸናፊ ሆነው ተመርጠዋል፡፡

የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ዕጩ ዳኞችን መልምሎ ለሹመት እንዲያቀርብ፤ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕዝደንቶች እና ም/ፕሬዝደንቶችን ለሹመት እንዲመለምል፤ የልዩ ልዩ የአስተዳደር ዘርፍ ክፍል ሃላፊዎችን እንዲሾም፤ ጉባዔው የሚተዳደርበትን ደንብ እንዲያወጣ፤ በከፍተኛ እና መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ፕሬዝደንቶች እና ም/ፕሬዝደንቶች እንዲሁም ዳኞች ላይ የሚቀርቡ የዲሲፕሊን ክስን እንዲመረምር፤ የዲሲፕሊን ክሶች የሚታዩበትን የስነስርዓት ደንብ እና ሌሎች መመሪያዎችን እንዲያወጣና አፈጻጸሙን እንዲከታተል፤ ለጉባዔው አባላት የሚከፈለውን አበል እንዲወስን ስልጣንና ተግባር የተሰጠው ነው፡፡

የፌ/ጠፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተቋማዊ መዋቅር ላይ ምክክር ተካሄደ
Next Article የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞችና የአስተዳደር ዘርፍ ክፍል ሃላፊዎች የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ
Print
2957