የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስርዓት የውጭ አማካሪ ምክር ቤት ዓመታዊ የውይይት መድረክ ተካሄደ
/ Categories: News

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስርዓት የውጭ አማካሪ ምክር ቤት ዓመታዊ የውይይት መድረክ ተካሄደ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስርዓት የውጭ አማካሪ ምክር ቤት ዓመታዊ የውይይት መድረክ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮች እና የአማካሪ ምክር ቤቱ አባላት በተገኙበት በቀን 20/05/2017 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ተቋሙ በመደበኛነት በሚያከናውነው እና እየተደረገ ባለው ሁለንተናዊ የለውጥ ስራ ላይ የአማካሪ ምክር ቤቱ የሚሰጠው ምክረ ሀሳብ እጅግ አጋዥ እና የተሻለ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት መሆኑን በመጥቀስ ይህንኑ የምክር ቤቱን እገዛ አጠናክሮ ለማስቀጠል ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የዳኝነት ስርዓት የዉጪ አማካሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ እስራኤል ተክሌ በበኩላቸው በምክርቤቱ የቆይታ ጊዜ የተከናወኑ ተግባራትና ወደፊት ሊከናወኑ በእቅድ የተያዙ ተግባራትን በመዘርዘር በቀጣይም የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን ለመሻሻል በሚረዱ ምክረ ሃሳቦችን በማመንጨት ፍርድ ቤቱን የማገዝ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

በመድረኩ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ዋና የሪፎርም ተግባራት ያሉበት ደረጃ እንዲሁም ከአማካሪ ምክር ቤቱ የተሰጡ ምክረ ሃሳቦችና አተገባበራቸው በተመለከተ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ዳኛ አበበ ሰለሞን እንዲሁም በአማካሪ ምክር ቤቱ በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ የተሰጡ ምክረ ሃሳቦችን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ዝርዝር የድርጊት መርሃ ግብር በፍርድ ቤቱ የሪፎርም አማካሪ አቶ ምስጋና ዴቢሳ ገለጻ ቀርቦ ውይይት ተደርጎባቸዋል ፡፡

በዉይይቱ ለቀረቡ ሃሳብና አስተያየቶች እንዲሁም ጥያቄዎች በፍርድ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ምላሽ የተሰጠባቸዉ ሲሆን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ አማካሪ ምክር ቤቱ ለፍርድ ቤቱ አያደረገ ላለው እገዛ ምስጋና አቅርበው በአባላቱ በተነሱ ህግን ከማሻሻል፣ አሰራርን ከማዘመንና የሰዉ ኃይልን ከማብቃት አንፃር ተቋሙ በርካታ ስራዎች እንደሚጠበቀዉ ገልፀዉ ለዚህም የምክር ቤቱ ሙያዊ እገዛ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም ለአንድ ዓመት ያህል የዳኝነት ስርዓት የዉጪ አማካሪ አባል በመሆን ሲያገለግሉ ለቆዩት የቀድሞ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ አሰግድ ጋሻዉ ከአማካሪ ምክር ቤቱ መሰናበታቸውን ተከትሎ ላበረከቱት አስተዋፅኦ የዕዉቅና ምስክር ወረቀት በክቡር ፕሬዝደንቱ የተበረከተላቸው ሲሆን በምትካቸው የቀድሞ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩና አሁን ላይ በህግ ማማከር አገልግሎት ላይ እየሰሩ የሚገኙት ወ/ሮ ሂሩት መለሰ ወደ አማካሪ ምክር ቤቱ ተተኪ አባል በመሆን ተቀላቅለዋል፡፡

Previous Article የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህንጻ ግንባታ ማስጀመሪያ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ
Next Article የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር የስራ አመራር ቦርድ አባላት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት አደረጉ
Print
1241