Monday, May 26, 2025 / Categories: News የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች የ2017 በጀት ዓመት የ9 ወር ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ተደረገ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች የ2017 በጀት ዓመት የ9 ወር ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም የፍርድ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና ክቡራን ዳኞች በተገኙበት ተደርጓል። መርሃ-ግብሩን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት መድረኩ ፍርድ ቤቱ በህዝብ አመኔታ ያለዉ ተቋም የማድረግ ራዕይ ተግባራዊ ለማድረግ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በጥራትና በሚፈለገዉ ፍጥነት መፈፀሙን ለመገምገም፣ የጎደለዉን በመለየት መፍትሄዎችን ለማስቀመጥ ዓላማ ያደረገ እና በቀጣይ የስራ ግዜ ለተሻለ አፈፃፀም የበለጠ ለመስራት የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች የ9 ወር የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ መልካም ዉጤቶች እንደታዩበት በሪፖርቱ የታየ ሲሆን በ9 ወር በዕቅድ ከተያዙት 15,883 መዛግብት ዉስጥ ለ13,237 መዛግብት እልባት በመስጠት አፈፃፀሙን 83 በመቶ ማድረስ ተችሏል። ይህ አፈጻጸም ካለፈዉ ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር በ1,925 መዛግብት ከፍ ያለ ነው፡፡ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በአጠቃላይ በ9 ወሩ በእቅድ ከተያዙት 106,449 መዛግብት ውስጥ 137,610 መዛግብት እልባት ያገኙ ሲሆን ይህ አፈፃፀም ካለፈዉ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ11,893 መዛግብት ብልጫ ያሳየ ሆኗል። በፍርድ ቤቶች በመዛግብትም ሆነ በሌሎች አስተዳደራዊ ድጋፎች የያዟቸዉን ዕቅዶች በማሳካት ሂደት ዉስጥ በየጊዜዉ መሻሻሎች እየታዩ ቢሆንም እየቀረቡ ካሉት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መዛግብት እና ተገልጋዮች ከተቋሙ ከሚጠብቁት አገልግሎት አንጻር አሁንም በከፍተኛ ትጋት እና የአገልጋይነት ስሜት መስራት እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ኢንስፔክሽን ግኝት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በሪፖርቱ ባለጉዳዮች የሚያቀርቧቸዉ ቅሬታዎች ይዘት፣ የችሎት ምልከታ ቅኝት ሪፖርትና በምልከታዉ የታዩ ክፍተቶች ከመፍትሄ ሃሳቦች ጋር ቀርበዋል፡፡ በመጨረሻም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች እየተተገበሩ ያሉትን የለዉጥ ስራዎች የበለጠ ለማጠናከር፤ የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ስርዓት የተደገፈ ለማድረግ የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ፕሮጀክቶች ወደ ትግበራ እየገቡ መሆኑ ተጠቁሞ ይህንኑ መጠቀም የሚያስችሉ የአጠቃቀም ክህሎት ስልጠናዎች በተከታታይ የሚሰጡ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ በቀረበዉ የ9 ወር አፈፃፀም ግምገማ መሰረት በመድረኩ ዉይይት በማድረግ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ሃሳብና ጥያቄዎች በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክቡር ፕሬዝደንት እና ሪፖርት አቅራቢዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በመጨረሻም ለበርካታ አመታት በዳኝነት ዘርፍ በቅንነትና በታታሪነት ሲያገለግሉ ለቆዩት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞ ዳኛ ወ/ሮ እትመት አሰፋ በተቋሙና በስራ ባልደረቦቻቸዉ የምስጋናና የእዉቅና ፕሮግራም ተደርጓል፡፡ Previous Article በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የለማ የኢፋይሊንግ፣ ኢሊቲጌሽንና ሰነድ ልውውጥ መተግበሪያ ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት ተካሄደ Next Article ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሴት ዳይሬክተሮችና ቡድን መሪዎች የአመራርነት ክህሎት ስልጠና ተሰጠ Print 1388