Monday, February 3, 2025 / Categories: News የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2017 የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት እቅድ አፈፃጸም ሪፖርት ግምገማ ተካሄደ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2017 የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት እቅድ አፈፃጸም ሪፖርት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮች፣ ክቡራን ዳኞች እንዲሁም የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በመክፈቻ ንግግራቸው የፍርድ ቤቱ ዋና ስራ የሆነዉ የዳኝነት ስራ ከዉጤት አንፃር ተገልጋይ የሚፈልገዉንና የሚጠብቀዉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ከፍጥነትና ከጥራት አንፃር መልስ መመለስ በሚያስችል መንገድ መፈፀም ካልተቻለ ህብረተሰቡ የሚፈልገዉን እርካታ ማምጣት አስቸጋሪ በመሆኑ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ፣ መልካም አፈጻጸሞች በማጠናከር እና ክፍተት የታየባቸውን አሰራሮች በመለየት የላቀ አፈፃፀም ላይ መድረስ ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በበጀት ዓመቱ የያዙትን አስራ ሶስት ግቦች ከማሳካት አንፃር መልካም ዉጤት መገኘቱ የተጠቀሰ ሲሆን የመዛግብት አፈፃፀምን በተመለከተ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ደረጃ በእቅድ ከተያዙት 64,703 መዛግብት 84,207 መዛግብት እልባት የተሰጠ ሲሆን ከዕቅዱ በላይ መፈጸም ተችሏል፡፡ ይህ አፈፃፀም ካለፈዉ ኣመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ20,734 መዛግብት ከፍ ያለ መሆኑ ተጠቅሷል። በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረጃ በእቅድ ከተያዙት 9,076 መዛግብት ዉስጥ ለ8,188 መዛግብት እልባት በመስጠት አፈፃፀሙን 90.3 በመቶ ማድረስ የተቻለ ሲሆን ይህ ካለፈዉ ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ998 መዛግብት ከፍ ያለ መሆኑ ተገልጿል ። በተጨማሪም አጠቃላይ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ዕልባት እንዲሰጥባቸው በዕቅድ ከተያዙ መዛግብት አንፃር ከፍ ያሉ አፈጻጸሞች እየታዩ ቢሆንም በየወቅቱ እየጨመረ ከመጣው የመዛግብ ፍሰት ጋር ተያይዞ እየቀረቡ ላሉ መዛግብት ዕልባት ከመስጠት አንፃር ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል። በሪፖርቱ በአፈፃጸም ወቅት የታዩ ጠንካራ ጎኖች፣ በድክመት የታዩ ችግሮችና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም የዳኞችና የችሎቶች የመዛግብት ስራ አፈፃፀም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ እስቲበል አንዱአለም ዳኞች በመደበኛና የእዕረፍት ጊዜያቸዉ የነበራቸዉን አፈፃፀም ፣የዳኞች የግል አፈፃፀም እና ለአፈፃፀማቸዉ መቀነስ ተጠቃሽ ምክንያቶችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም በተመሳሳይ ሁኔታ ከዳኝነት ስራ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸዉ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሬጅስትራር ጽ/ቤት፣ የዳኝነት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት እንዲሁም የኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ሪፖርት በየስራ ክፍሎቹ ሃላፊዎች ቀርቧል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ የ2017 መጀመሪያ መንፈቅ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ጥሩ አፈፃፀም የታየበት መሆኑን ገልፀዉ ለዳኝነት ስራ አገልግሎት አሰጣጥ ቁልፍ የሆኑ ስራ ክፍሎች ላይ ልዩ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ በትኩረት በመስራት ተገልጋዩ ማህበረሰብ የሚፈልገዉን አገልግሎት እንዲያገኝ በሚያስችል መንገድ መሰራት እንዳለበት ጠቅሰዉ በግምገማዉ ለተነሱት ችግሮች አንድም አሰራርን የሚያዘምኑ አሰራሮችን በመዘርጋት በሌላ በኩል ደግሞ ተቋሙ ያሉትን የአሰራር ስርዓቶች በተገቢዉ መንገድ በመተግበር ለመፍታት በጋራ መስራት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ተኽሊት ይመሰል በዳኝነት ስነ-ምግባር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ አጭር ፅሁፍ ቀርቧል፡፡ በአጠቃላይ በቀረበው የመንፈቅ ዓመቱ አፈፃፀም ግምገማ መሰረት በመድረኩ ዉይይት የተደረገባቸዉ ሲሆን ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛ አመራሮችና ሪፖርት አቅራቢዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ Previous Article የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር የስራ አመራር ቦርድ አባላት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት አደረጉ Next Article "ስነ ምግባራዊ አመራርነት ለተቋማዊ ተልእኮ ስኬት" በሚል መሪ ቃል ለፌደራል ፍርድ ቤቶች መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ተሰጠ Print 1156