Thursday, September 17, 2020 / Categories: News የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባዔ 5ኛ ዓመታዊ ጉባዔ የአቋም መግለጫ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባዔ በፌዴራል ፍ/ቤቶች አዋጅ 25/88 ከአንቀጽ 31-34 በተደነገገው መሰረት የተቋቋመና በዳኝነት ሥራ አስተዳደር ረገድ በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ ተወያይቶ መፍትሔ የመስጠት፤ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አሰራርን ለማሻሻል የሚረዱ መመሪያዎችና ውሳኔዎችን የማሳለፍ፤ አዳዲስ ሕጎች እንዲወጡ ወይም ነባር ሕጎች እንዲሻሻሉ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሃሰብ የማቅረብ፤ የዳኝነት ስራ አካሄድን ለማቀላጠፍና ለማጠናከር የሚረዱ ሌሎች ተግባራትን የማከናውን እና ለጉባዔው ስራ አፈጻጸም አስፈላጊውን ደንብ የማውጣት ስልጣንና ተግባር የተሰጠው ጉባዔ ነው፡፡ በዚህም መሰረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባዔ 5ኛውን ዓመታዊ ጉባዔ ዛሬ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በፌዴራልና በክልል ፍርድ ቤቶች ተቋማዊና ዳኝነታዊ ነጻነት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡ ጉባዔው ባካሄደው ውይይት የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች በነጻነትና በገለልተኝነት ዳኝነት የመስጠት ህገመንግስታዊ ሃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት መሆናቸው በውይይቱ ተገልጿል፡፡ የዳኝነት ተጠያቂነት የዳኝነት ነጻነት ዋስትና መሆኑንም ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ ነው፡፡ በሃገራችን ከመጣው የለውጥ እንቅስቃሴ በኋላ በፌዴራልና በክልል ፍርድ ቤቶች የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቀሴዎች መኖራቸውንና የተወሰኑትም ቢሆኑ ተግባራዊ መሆን መጀመራቸውን መገንዘብ ተችሏል፡፡ የዳኝነት ነጻነትን ለማረጋገጥ ከተሰሩ ስራዎች መካከልም የፍርድ ቤቶች አደረጃጀትና የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አዋጆችን የማሻሻል ስራዎች በሂደት ላይ መሆናቸው፤ በዚህም አስተዳደራዊ እና የበጀት ነጻነት መጎናጸፍ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች መካተታቸው፤ እንዲሁም የዳኞችን ግለሰባዊ ነጻነት ለማስጠበቅም ያለመከሰስ መብት የህግ ድጋፍ እንዲኖረው መደረጉ፤ ከዚህ ጎን ለጎን የዳኝነት ነጻነት ዋስትና የሆነው የዳንነት ተጠያቂነት ስርዓት መዘርጋት የሚያስችሉ አንቀጾች እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ የዳኞችን ግለሰባዊ ነጻነት ከሚያስጠብቁ ጉዳዮች መካከልም በፌዴራልና በተወሰኑ ክልሎች የደሞዝ ማሻሻያ መደረጉ፡፡ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች የመኖሪያ ቤት እንዲያገኙ መደረጉ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንዲጠበቁላቸው ጥረቶች መደረጉ ታይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ዳኞች ከህግ አውጪውም ሆነ ከአስፈጻሚው አካል ሊደርስ ከሚችል ተጽእኖ ነጻ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸው ውሳኔዎችም መከበርና መፈጻም አለባቸው፡፡ ዳኞች ከሚሰጣቸው ውሳኔዎች ጋር ተያይዞ ከማንኛውም ስጋት ነጻ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር በአንዳንድ ክልሎች ፍርድ ቤቶች የበጀት፤ የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችን ከማስተዳደር አንጻር ችግሮች ያሉባቸው መሆኑ ተነስቷል፡፡ በምክር ቤቱ የተፈቀደ በጀትን የመከልከል ችግሮችም እንዳሉ ተነግሯል፡፡ በተወሰኑ ክልሎች ደግሞ በበጀት እጥረት ምክንያት የደሞዝ ማሻሻያ አለመደረጉ እና ተመጣጣኝ ክፍያ መርህን ያልተከተለ የደሞዝ ማስተካከያ መደረጉም ከተነሱ ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ከዳኞች ግለሰባዊ ነጻነት ጋርም ተያይዞ በተወሰኑ ክልሎች ዳኞች በሰጡት ውሳኔ በፖሊስ የመታሰር፤ ባልታወቁ ሰዎች የመደብደብ፤ በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ ተኩስ በመክፈት ጫና ለማሳደር መሞከር፤ በማህበራዊ ሚዲያ ዳኞች ከህግ ውጪ እንዲወስኑ በተለያዩ ግለሰቦችና ኢ-መደበኛ ቡድኖች ጫና ማሳደር እና የመሳሰሉት ሁኔታዎች ተስተውለዋል፡፡ እነዚህን በፈጸሙ ግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ ተገቢውን ህጋዊ ምርመራ አድርጎ ወደ ህግ በማቅረብ በኩል ክፍተቶች ታይተዋል፡፡ በተጨማሪም ቁጥጥር ሊደረግባቸው የማይችሉ ሚዲያዎች የሚያሰራጯቸው አሉታዊ ይዘት ያላቸው መረጃዎች በፍርድ ቤትና በዳኞች ላይ ተጽዕኖ መፍጠራቸውም እንደዚሁ ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ በመነሳት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባዔ 5ኛ ዓመታዊ ጉባዔ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ በማውጣትም ስብሰባውን አጠናቋል፡፡ 1. የዳኝነት ነጻነት መኖር በህግ ማዕቀፍ ብቻ የሚረጋገጥ ባለመሆኑ የዳኝነት ነጻነት መከበር በተግባርም ጭምር መታየት ይኖርበታል፡፡ ለዚህም የህግ አውጪውም ሆነ የአስፈጻሚው አካል በህገ መንግስትና ተያያዥ ህጎች መሰረት ለዳኝነት ነጻነት መረጋገጥ እና አገልግሎት መሻሻል አስቻይ የሆነ በጀት የሃገሪቱ አቅም በሚፈቅደው መጠን መመደብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ 2. የዳኝነት ነፃነትን ማስጠበቅ በዋነኝነት የዳኞች ኃላፊነት ቢሆንም የመንግስት አስፋፃሚ አካል፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ ሲቪል ማህበራት እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት፤ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና የመንግስትን ቀጠይነት ለማረጋገጥ እንዲያስችል የዳኝነት ነጻነት እንዲከበር የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ 3. የዳኝነት ነጻነት በዳኞች የሚሰጡ ውሳኔዎች በህገመንግስቱ ከተቋቋመ የመንግስት ተቋም የሚሰጡ ውሳኔዎች በመሆናቸው ትእዛዛቸውና ውሳኔያቸው መከበርን ግድ ይላል፡፡ የዳኝነት ነጻነትን የተመለከቱ የህግ ማዕቀፎች መኖር አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ የመንግስት አካላትን ጨምሮ ሌሎች ወገኖች በፍርድ ቤት የሚሰጡ ውሳኔዎችን በማንኛውም አካል ምርመራ ሳይደረግባቸውና ሳይሸራረፉ ማክበር እና ተግባራዊ ማድረግም ይኖርባቸዋል፡፡ 4. በህገመንግስታችን መግቢያ እንደተገለጸው በሃገራችን አንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመመስረት የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች ወሳኝ ድልድዮች ናቸው፡፡ በስራ ረገድም በበርካታ ሁኔታዎች ይገናኛሉ፡፡ የሚመሩበት የሙያ መርህና የስራ ባህሪያቸውም እጅግ ተመሳሳይ በመሆኑ የዳኞችን ግለሰባዊ ነጻነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ የደመወዝ እና የጥቅማጥቅም ፓኬጆች ምክንያታዊና ነባራዊ ሁኔታውን ከግምት ያስገባ እንዲሆኑ አመራሩ በቀጣይነት በልዩ ትኩረት የሚሰራበት ጉዳይ ይሆናል፡፡ 5. የዳኝነት እና የዳኞች ነጻነት የህግ የበላይነት ቁልፍ ማዕዘን ነው፡፡ በየትኛውም ቦታ የሚያገለግሉ ዳኞች የስራ ነጸነት መከበር አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ዳኞች ሁሉ በጋራ መቆምና ሙያዊ መደጋገፍን ማሳየት ሃላፊነታችን ነው፡፡ የዳኞች በባለጉዳይም ሆነ በመንግስት አካላት መደፈር በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው፡፡ መንግስት የዳኝነት ነጻነትን ለማረጋገጥ ያለውን ፍላጎትና ቀርጠኝት በተለያየ ሁኔታ ቢያሳይም በመንግስት የታችኛው መዋቅር ያሉ ግሰቦች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ባልተገባ መንገድ በመጠቀም በዳኝነት ነጻነት ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተጽእኖ በጋራ የምንታገለው ይሆናል፡፡ መንግስትም በህግ የበላይነት መከበር ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች እየተስፋፉ እንዳይሄዱ ከላይ በተጠቀሱትና መሰል ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ምርመራ በማድረግ ለይቶ ወደ ህግ በማቅረብ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡ 6. የዳኝነት ተጠያቂነት የዳኝነት ነጻነት ዋስትና ነው፡፡ ዳኞች ስህተት ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ውሳኔያቸው በይግባኝ ሊሻር ይችላል፡፡ ከዚህ አልፎ የተሰጣቸውን የዳኝነት ስልጣን ባልተገባ መልኩ በመጠቀም የዲሲፕሊን ጥፋት የሚፈጽሙ ዳኞች ተጠያቂ የሚሆኑበት ስርዓት አለ፡፡ የዳኝነት ነጻነትን ሚዛን መጠበቅ የሚያስችል የተጠያቂነት ስርዓት መዘርጋት በፍርድ ቤቶች በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም በአንድ ሃሳብ የተቀበልነው ጉዳይ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃንና መስፈርትን የጠበቀ የዳኝነት ተጠያቂነት ስርዓት ለመዘርጋት የጀመርናቸውን ጥረቶች አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል፡፡ 7. የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ይታወቃል፡፡ መንግስት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚወስዳቸው ሌሎች እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው በፍርድ ቤቶች በኩል ወረርሽኙ ያለመገታቱን በመገንዘብ የተጀመሩትን የጥንቃቄ እርምጃዎች መቀጠል ይኖርብናል፡፡ 8. ጉባዔው የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶችን የዳኝነት አሰራር ለማሻሻል የሚረዱ መመሪያዎችና ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ የተሰጠውን ስልጣን ተግባራዊ ለማድግ በፌዴራልና በክልል ፍርድ ቤቶች ያሉትን የጋራ ችግር በመለየትና ምክረ ሃሳብ በማቅረብ ድጋፍ የሚያደርግ ኮሚቴ ተቋቁመዋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባዔ 5ኛ ዓመታዊ ጉባዔ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. Previous Article የዳኝነትና የዳኞች ነጻነት መከበር ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ቁልፍ ማዕዘን ነው Next Article የፍ/ቤቱን ሴት ሰራተኞች ማብቃትና ሃላፊነታቸዉን በብቃት መወጣት የሚያስችሉ ድጋፎችን ማመቻቸት እንዲሁም ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር አስፈላጊነት ተጠቆመ፡፡ Print 2204