Monday, February 9, 2026 / Categories: News የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ 2018 ዓ.ም የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የስራ አፈፃጸም ሪፖርት የውይይት መድረክ ተካሄደ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2018 የመጀመሪያዉ መንፈቅ ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት የውይይት መድረክ የፍርድ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳኞች እና የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም ተደርጓል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ መድረኩን በመክፈቻ ንግግር ሲያስጀምሩ፤ የዳኝነት ስርዓቱ ሁለንተናዊ ለዉጥ ለማምጣትና የተገልጋይን እርካታ ለማሳደግ ተቋሙ በሚያደርገዉ የለዉጥ ጉዞ ዉስጥ ባለፈዉ ስድስት ወራት ዉስጥ የተከናወኑ ስራዎችን ከመገምገም ባለፈ የታዩ ክፍተቶችን በመለየት፣ ለማረምና መልካም ተሞክሮዎችን ለማስፋት ብሎም የተገኙ ስኬቶችንም ለማክበር ዓላማ ያደረገ መድረክ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አክለውም የዳኝነት አግልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ስራዎች በተገልጋዮች ዘንድ ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆኑን በተለይም ከዲጂታል የዳኝነት አገልግሎት አንጻር የዋይድ ኤርያ ኔትወርክ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ፕሮጀክት መጠናቀቅና ዝርጋታውን ተከትሎ እየተጠናቀቀ ያለው የተቀናጀ የፍርድ ቤት አስተዳደር መረጃ ስርዓት(ICMIS) ያለበት የአፈጻጸም ደረጃ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይም ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለዉና ተደራሽ የሆነ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል በትብብርና በተቀናጀ ሁኔታ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በመድረኩ አጠቃላይ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የ2018 ዓ.ም የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የዳኞች ስራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የዳኝነት ኢንስፔክሽን ጥናት ሪፖርት፣ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር አፈጻጸም ሪፖርት እንዲሁም የአስተዳደር ክፍሎች የስራ አፈጻጸም ሪፖርቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በመንፈቅ ዓመቱ በፌደራል ፍርድ ቤቶች እልባት እንዲያገኙ በእቅድ ከተያዙ 58,236 መዛግብት መካከል 81,730 መዛግብት እልባት በመስጠት ከእቅድ በላይ መስራት ተችሏል፡፡ አፈጻጸሙ ለየፍርድ ቤቶች ከተያዘዉ ዕቅድ አንፃር ሲታይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለ7,960 መዛግብት እልባት ለመስጠት ታቅዶ 8,324 መዛግብት እልባት በማግኘታቸዉ አፈጻጸሙ 104.5% ሊደርስ በመቻሉ ካለፈዉ ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በቁጥር 125 መዛግብት የአፈጻጸም ብልጫ አሳይቷል፡፡ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለ10,204 መዛግብት እልባት ለመስጠት ታቅዶ 11,452 መዛግብት እልባት በማግኘታቸዉ አፈጻጸሙ 112% ፣ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለ40,072 መዛግብት እልባት ለመስጠት ታቅዶ 61,954 እልባት በማግኘታቸው አፈጻጸሙ 155% መድረሱን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ባደረጉት ንግግር፤ በመንፈቅ ዓመቱ በሁሉም መስክ የተሰሩ ስኬታማ ተግባራት የሚደነቁ መሆናቸውን አንስተው የግልጽ ችሎት አገልግሎቶችን በማጠናከር፣ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ በተለይም እግድ ያለባቸው እና ውዝፍ መዛግብትን ቅድሚያ ሰጥቶ በመስራት፣ በሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጡ ውሳኔዎች ወጥነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት እንዲሁም ሌሎች የፍርድ ቤቱ አገልግሎቶች ላይ ከተገልጋይ የሚሰጡ አስተያየቶችና ቅሬታዎችን ተገቢውን ምላሽ በመስጠት እና ቀጣይነት ያላቸውን የማሻሻያ ስራዎች በጥብቅ ስነ ምግባር በመፈጸም ለተሻለ አፈጻጸም መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ Previous Article የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንቶችን እና የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመት አፀደቀ Next Article ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንቶች የፌደራል ፍርድ ቤቶች የሪፎርም ተግባራት ላይ ገለጻ ተደረገ Print 494