የፌዴራል ፍ/ቤቶች ከፍተኛ አመራር እንዲያጸድቅ በቀረቡለት ሁለት ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ተወያየ
/ Categories: News

የፌዴራል ፍ/ቤቶች ከፍተኛ አመራር እንዲያጸድቅ በቀረቡለት ሁለት ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ተወያየ

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንቶችና ም/ፕዝደንቶች ሚያዚያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ እንዲያጸድቃቸው በቀረቡለት የፍትሃብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ረቂቅ መመሪያ እና የተሸሻለውን የCCMS (Court Case Management System) ለመተግበር የሚያስችል የስራ መዘርዝር እና ፍሰት የሚገልጽ ሰነድ ላይ ተወያየ፡፡

የፍርድ ቤቶቹ ከፍተኛ አመራር ጉባዔ በተለይ በፍትሃ ብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ላይ ሰፊ ውይይት ያካሄደ ሲሆን መመሪያው የሚቀርቡ ጉዳዮችን በዓይነት የሚለይና በተቀመጠላቸው ውሳኔ የማግኛ ጊዜ ግደብ ውስጥ እልባት እንዲያገኙ የሌሎች ሃገራትን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ ከፍርድ ቤታችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የተዘጋጀ መመሪያ መሆኑን ገምግሟል፡፡

በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ላይ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ተስፋ የተጣለበት የጉዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያን መተግበር የዳኝት አገልግሎት አሰጣጡ ተገማችና ቀልጣፋ በውጤቱም የፍርድ ቤቶችን አመኔታ ከፍ የሚያደርግ እንደሆነም ታምኖበታል፡፡

የጉዳዮች ሂደትና እልባት መስጫ ጊዜ መጓተትን ማስቀረት፤ ዜጎች በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ያላቸው አመኔታና እርካታ መጨመር፤ ለጉዳዮች እንደየ መደባቸውና ተናጠል ባህሪያቸው ተመጣጣኝ የሆነ ትኩረት መስጠት፤ ለሁሉም ተከራካሪ ወገኖች የጉዳዮች ሂደትና እልባት መስጫ ጊዜን ተገማች ማድረግ፤ እና በጉዳዮች ሂደት ውስጥ የሚከናወኑ ድርጊቶች ክንውን ጥራት መጨመር የረቂቅ መመሪያው መዳረሻ ግቦች ናቸው፡፡

ከመመሪያው አተገባበር ጋር ተያይዞ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን እና ተግዳሮቶችን ለመቀነስ ያስችል ዘንድ በውይይት መድረኩ ትኩረት የተሰጣቸው በመመሪያው የተቀመጡ ጥቂት ድንጋጌዎች እና አፈጻጸሙን የሚከታተለው የስራ ክፍል አደረጃጀት ላይ ማስተካከያ ተደርጎና የአርትኦት ስራ ተጠናቆ አመራሩ ለማጽደቅ እንዲቀርብለት የስራ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

አመራሩ በሁለተኛው አጀንዳ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ላለፉት 15 ዓመታት ባልተሟላ ሁኔታ ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው የፍርድ ቤት ጉዳዮች አስተዳደር ስርዓትን ለማሻሻል እና በሶስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ወጥ በሆነ መልኩ ለመተግበር የሚያስችል የስራ መዘርዝር እና ፍሰት የሚገልጽ ሰነድ ላይ ተወያይቷል፡፡

የተሸሻለው የCCMS (Court Case Management System) 6 ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል ሲሆን በዳኝነት አለገልገሎት አሰጣጥ ሂደት ላይ የመዛግብት አያያዝ፤ መረጃ ቅብብሎሽና ተደራሽነት እንዲሁም በእያንዳንዱ ሁነት ያለውን አላስፈላጊ ሂደት የሚያሳጥር ሲሆን በተቋም ውስጥ ያለውን ኔትወርክ በመጠቀም አገልግሎ የሚሰጥ በመሆኑ በእያንዳንዱ ምድብ ችሎት ዲጂታል ሰነድ ማከማቻ የሰርቨርና ኔትወርክ፤ የወረቀት ሰነዶችን ወደ ዲጂታል ለመቀየር በርካታ የስካኒንግ ማሽን (Heavy duty Scanning Machines) እና ተስማሚ የሆነ የሰው ሃይል አደረጃጀት እንደሚያስፈልገው በውይይቱ ተነስቷል፡፡ በዳኞች፣ በረዳት ዳኞች እና ሬጂስትራሮች እና ሌሎች ላይ ተጨማሪ የስራ ጫና ሊፈጥር እንደሚችልም ተነግሯል፡፡

የተሸሻለው ስርዓት የፍርድ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ ሂደትን በከፊል ወረቀት አልባ ያደርጋል የተባለ ሲሆን ሰነዱን ወደ ተግባር ለመለወጥ ከፍተኛ አስተዳደራዊ ድጋፍ እና ውሳኔ እንዲሁም በአሰራሩ ውስጥ ሚና ያላቸው ዳኞች፤ ረዳት ዳኞች፤ ሬጂስትራሮችና ሌሎች ደጋፊ ባለሙያዎችን ማብቃት የሚጠይቅ በመሆኑ ተጨማሪ ውይይት እንዲደረግበት የስራ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡

በከፍተኛ አመራሩ ውይይት የተደረገባቸው ሁለቱ ርዕሰ ጉዳዮች በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከተያዙ አብይ የማሻሻያ ስራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article የስትራቴጂካዊ ዕቅድ ዝግጅት አማካሪ ድርጅት ዕቅድ ዝግጅቱ ያለበትን የስራ ደረጃ ለዐብይ ኮሚቴው ገለጸ
Next Article የአዋጅ መሻሻልን ተከትሎ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የችሎት አደረጃጀትና የዳኞች አሰያየም ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት ለተጨማሪ ግዓብት ለውይይት ቀረበ
Print
525