Saturday, June 11, 2022 / Categories: News የፍርድ ቤቱን የአስተዳር ሰራተኞች አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነት የሚያጎለብቱ ስልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ የፍርድ ቤቱን የአስተዳር ሰራተኞች አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነት የሚያጎለብቱ ስልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ የፍርድ ቤት የአስተዳር ሰራተኞችን አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነት የሚያጎለብቱ ስልጠናዎችን የመስጠት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ፡፡ ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ ይህን የገለጹት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ዘርፍ የጽ/ቤት ሃላፊዎች፣ ዳይሬክተሮችና ቡድን መሪዎች በተዘጋጀ ስልጠና ማጠቃለያ ላይ በሰጡት የስራ መመሪያ ነው፡፡ ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በንግግራቸው ፍርድ ቤቱ የጀመራቸውን የማሻሻያ ስራዎች ከዳር ለማድረስ የመካከለኛ አመራሩ ድርሻ የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ይህንንም ድርሻቸውን ተገንዝበው የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አስፈላጊው የክህሎት እና እውቀት ማጎልበቻ ስልጠናዎች ተጠናክረው ይሰጣሉ ያሉ ሲሆን ይህም ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን አገልግሎት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ወረቀት አልባ ለማድረግ እየተተገበረ ያለውን ፕሮጀክት ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችል እንደሚሆኑም ጠቁመዋል ፡፡ መካከለኛ አመራሮች፤ ከፍተኛ አመራሩ የሚያመነጫቸውን ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ወደ ተግባር ከሚለውጡና ከሚፈጽሙ ባለሙያዎች ጋር የሚያገናኙ ድልድዮች ናቸው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ በፍርድ ቤቱ የተጀመሩ እና በሂደት ላይ ያሉ የማሻሻያ ስራዎች የታለመላቸውን ውጤት እንዲያስገኙ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ በፍርድ ቤቱ ኮርት ማናጀር አማካኝት የተዘጋጀው የ3 ቀን የመካከለኛ አመራሮች ስልጠና ተቋማዊ ተግባቦትን እና የመረጃ ልውውጥ ሰርዓትን በማጠናከር ተቋማዊ ተልኮን ከፍተኛ ደረጃ መወጣት የሚያስችል ግንዛቤን የሚያጎልበት ዓላማ ያለው ነው፡፡ ስልጠናው “መራር እና ተግባቦት (Leadership and Communication)” እንዲሁም “ውጤታማ ተቋማዊ አፈጻጸምን ማሳደግ (Promoting Effective Organizational Performance)” በሚሉ ሁለት አንኳር ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን የመካለኛ እና መጀመሪያ ደረጃ አመራሮች ከከፍተኛ አመራሩ እና ከባለሙያዎች ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባ ተግባቦት፣ የአመራር ከህሎት እና ተቋማዊ ግቦችን ለማሳካት የሚኖራቸውን ሚና ማስገንዘብ አስፈላጊነ ታምኖበት የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የአመራር እና ተግባቦት ስልጠናው በዶ/ር ሳለአምላክ ሞላ የተሰጠ ሲሆን በአመራርነት ርዕስ ስር የአመራር ምንንነት፣ ባህሪያት፣ ዘዬዎች፣ ስልቶች፣ እና ዓይነቶችን፤ በተግባት ርዕሰ ጉዳይ ስር የተቋማዊ ተግባቦት ምንነት፣ ከአመራርነት ክህሎቶች መካከል አንዱ የተግባቦት ክህሎት ስለመሆኑ፣ ተቋማዊ ተግባቦ አይነቶች፣ የተግባቦት አላማዎች፣ የተግባቦት ሂደት፣ ስልቶች፣ የተግባቦት ደንቃራዎች እና ተጽእኖዎችን የመቀነሻ ስትራቴጂዎችን አስመልክቶ በገለጻ፣ በቡድን ስራ እና በሰርቶ ማሳያ ስልቶች በጠቀም የስልጠና ተሳታፊዎችን ግንዛቤ እና ክህሎት ማዳበር ተችሏል፡፡ ይህንንም ተከትሎ አቶ አዱኛ ነመራ ውጤታማ ተቋማዊ አፈጻጸምን ማሳደግ በሚል ርዕስ ስልጠናው የቀጠለ ሲሆን በስልጠናው ከዓለም ዓቀፍ ዘላቂ ልማት ግቦት በመነሳት የሃገራችንን የ10 ዓመት የልማት እቅድን በመዳሰስ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስትራቴጂያዊ ዕቅድን በወፍበረር በመቃኘት ያላቸውን ትስስር አሳይቷል፡፡ ስትራቴጂያዊ እቅዱን በመተግበር ድርሻ ያላቸው በየትኛው ደረጃ ላይ ያሉ አመራሮች ሊወጡት ስለሚገባ የአመራር ሚና እና ተግባራትንም አስገንዝቧል፡፡ በገለጻው የአመራር ወሰንን ማስፋት፣ የተሰጠ ተልዕኮን ለመወጣት ከሌሎች አካላት ጋር በጋራ የሚሰሩ ተግባራትን መለየት፣ ግንኙነት መፍጠር፣ የጋራ ድርሻን መወጣት የጋራ ግብን ለማሳካት ያለውን አስፈላጊነት ማስጨበጥ ተችሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር ማቀድ፤ መተግር፤ መቆጣጠርና መመዘን እና በየምዕራፉ ስለሚደረጉ የአፈጻጸም ሪፖርቶች ይዘትና አቀራረብ ሰፋ ያለ ገለጻ ተሰጥቷል፡፡ የስልጠና ተሳታፊዎችም በማጠቃለያው ላይ በሰጡት አስተያየት በስልጠናው ያገኙት ግንዛቤ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ዓቅም የፈጠሩላቸው፤ ክህሎታቸውን ማዳበር የሚችሉባቸውን ስልቶች ያገኙባቸው፣ እንዲሁም ጽንሰ ሃሳቦች እና ልምዶችን የቀሰሙባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ስድስት መቶ የሚሆኑ የአስተዳደር ሰራተኞችን በአራት ዙር መልካም ስነ-ምግባርን ጠብቀው እንዲያገለግሉ የሙያ-ስነምግባር (work ethics)፤ ጊዜያቸዉን ባግባቡ በመጠቀም የአገልግሎት ቅልጥፍናን እንዲያሳድጉ የጊዜ አጠቃቀም (time management)፤ ሰራተኞች ከባለጉዳዮች ጋር ያላቸዉን መልካም ግንኙነት በማሻሻል የአገልጋይነት ስሜትን ለመፍጠር የደንበኛ አያያዝ (customer service) እና የጸረ-ሙስና ተግባራትን ለማጠናከር በህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሙስናን መዋጋት (combating corruption in public organizations) በሚሉ ርእሰች ላይ ስልጠና መስጠቱ ይታወሳል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት Previous Article በአስተዳደር ዘርፍ የፍርድ ቤቱን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሰራተኞውን የመፈጸም ዓቅም ለማጎልበት የሰራ መሆኑ ተገለጸ Next Article በሃገራችን የሰብዓዊ መብትን ለመጠበቅም ሆነ ለማስከበር በቂ የህግ ማዕቀፍ ያለ መሆኑ ተገለጸ Print 1754