የፍርድ ቤቱ ሠራተኞች ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን አከበሩ
/ Categories: News

የፍርድ ቤቱ ሠራተኞች ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን አከበሩ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ23ኛ ጊዜ በመከበር ላይ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በሀገራችን ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ “በትዉልድ ቅብብሎሽ ኢትዮጵያ ትፀናለች” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኝ ሲሆን ቀኑ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠራተኞች ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ/ም በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ፡፡

በዓሉ በፍርድ ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ ሲከበር የፍርድ ቤቱ ሴቶችና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ወርቅነሽ በቀለ ባደረጉት የመክፈቻ ላይ ንግግር እንደገለጹት ከሰባት ቢሊዮን በላይ ከሚገመተዉ የዓለም ህዝብ መካከል የወጣቱ ቁጥር 1.8 ቢሊዮን እንደሚደርስና ከዚህ ውስጥ 90 ከመቶ የሚሆነዉ ወጣት በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት እንደሚገኝ ጠቅሰው ከሀገራችን የህዝብ ብዛትም 31.8 በመቶ ያህሉ ከፍተኛ አቅም ያለዉ አምራች ኃይል የሆነዉ የወጣቱ ክፍል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስተባባሪነት አምራች የሆነዉን ይህን የሕብረተሰብ ክፍል ትኩረት በመስጠት በሁሉም የድርጅቱ የልማትና የእድገት አጀንዳዎች በማካተት ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ በሁሉም ሀገራት በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በፍርድ ቤቱ ዉስጥ የሚሰሩ ወጣት ሰራተኞች ተቋሙ በሚያደርገዉ ማናቸዉም እንቅስቃሴ ዉስጥ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ተገቢዉን ኃላፊነት እንዲወጡና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸዉን ማረረጋገጥ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በፍርድ ቤቱ የሴቶችና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ የሆኑት የአቶ አሌክሳንደር አዳም በስብዕና ግንባታ ላይ ስልጠና የሰጡ ሲሆን እርሳቸው እንዳሉት ወጣቱ ትዉልድ በሀገርና በተቋማት ግንባታ ላይ ያለዉ ገንቢ ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን አገልግሎት አሰጣጥን “ሰዎች እንዲያደርጉልኝ የምፈለገዉን እኔም ለሌሎች ማድረግ ይገባኛል” በሚል መርህ ማከናወን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ወጣቱ ከምንም ነገር በላይ በራስ የመተማመን አቅሙን አጎልብቶ ለራሱ ተገቢውን ግምት በመስጠት ህዝብና ሀገር የጣሉበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አስምረዉበታል፡፡

በመጨረሻም ከኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር 70 በመቶ ያህሉ ወጣት በሆነበት ሁኔታ ይህን ዕድል ወደ ዉጤት ለመቀየር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ርብርብ ከፍተኛ መሆን እንደሚገባውና ወጣቱ ትዉልድ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎዉን ከፍተኛ ዉጤት በሚያስገኝ መልኩ የማከናወን ኃላፊነት እንደተጣለበትም የሴቶችና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

የፌደራል ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ዳኞች በማያቋርጥ ሒደት ብቃታቸውን ሊያሳድጉና በሥልጠና ሊያልፉ እንደሚገባ ተጠቆመ
Next Article የሌሎችን  የሥነምግባር ችግር ከሚዳኘው የዳኝነት ተቋም የላቀ የሥነምግባር ደረጃ እንደሚጠበቅ ተጠቆመ
Print
55