Saturday, February 19, 2022 / Categories: News የፍርድ ቤቱ አስተዳደር ዘርፍ አፈጻጸም ከፍተኛ መሻሻል ያሳየ መሆኑ ተገለጸ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ዘርፍ የስራ ክፍሎች አፈጻጸም ከፍተኛ መሻሻል ያሳየ መሆኑን የ2014 መጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ገምገማ ውጤት ማመልከቱ ተገለጸ፡፡ በዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ማጠቃለያ መድረኩ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ የተገኙ ሲሆን የቀረበውን የማጠቃለያ ሪፖርት መሰረት በማድረግ በሰጡት አስተያየት በአስተዳደር ዘርፉ እየተመዘገበ ያለው አመርቂ አፈጻጸም በፍርድ ቤቶች እየተከናወኑ ያሉ የማሻሻያ ስራዎች ፍሬ እያፈሩ ስለመምጣታቸው ያላቸውን እርግጠኝነት ከፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ በሁለት ቡድን ተከፍሎ የተካሄደው የአስተዳደር ዘርፍ የስራ ክፍሎች የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ማጠቃለያ ሪፖርት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስትራቴጂክ ስራ አመራር ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ አቤል ጌትነት የቀረበ ሲሆን ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ በሰጡት ማብራሪያ የአፈጻጸም ውጤቱ አውንታዊ መሻሻል የታየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በማጠቃለያ መልዕክታቸው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌደራል ፍርድ ቤቶችን በበላይነት የመምራትና የማስተባበር ሕገመንግስታዊ ኃላፊነት ያለበት ተቋም እንደመሆኑ መጠን የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች በመተግበር የአርአያነት ሚናውን መጫወት አለበት ብለዋል፡፡ በተገኘው አበረታች ውጤት መዘናጋት ሳያስፈልግ የተጀመሩት የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በቅርቡ ተግባራዊ መደረግ በጀመረው የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ መሠረት ጉዳዮች በግልጽ ችሎት እንዲታዩ ከመከታተልና ከመደገፍ አንጻር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረዉ መቀጠል አለባቸው ብለዋል፡፡ ክብርት ፕሬዝደንቷ ካላፈው ዓመት የተሻገሩ ውዝፍ መዛግብት ለመመሪያው አተገባበር እንቅፋት መሆናቸውን ጠቁመው እነዚህን መዛግብት በልዩ ሁኔታ ለማስተናገድ በዳኞች አስተዳደር በኩል መፍትሔ እየተፈለገለት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ስትራቴጂያዊ ዕቅድ የተቀመጡ የጋራ ራዕያችንን እና እሴቶቻችንን መሠረት በማድረግ የምናከናውናቸው ተግባራት አሁን በውጭ አማካሪ ድርጅት የጥናት ውጤት የተረጋገጠዉን የባለጉዳዮች እርካታ ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችሉ መሆን አለባቸው ያሉት ክብርት ፕሬዝደንቷ የህዝብን አመኔታ ለማጎልበት የሁሉም ሥራ ክፍሎች ኃላፊዎችና ሠራተኞች ወጥና የጠራ ግንዛቤ ይዘው ለጋራ ውጤት የመስራታቸውን አስፈላጊነት በአጽንኦት አብራርተዋል፡፡ በመጨረሻም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር አቶ ቦጃ ታደሰ በክብርት ፕሬዝደንት የተሰጡት ጥቅል የስራ አቅጣጫዎች በተሳካ ሁኔታ ሊፈጸሙ የሚችሉበትን ዝርዝር የስራ መመሪያ በመስጠት የስራ አፈጻጸም ማጠቃለያ ውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡ ነጻና ገለልተኛ ፍርድ ቤት ለህግ የበላይነት! የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፣ ዓ.ም Previous Article ፍርድ ቤቱ ለአራት ክልሎች ጠቅላይ ፍ/ቤቶች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ Next Article ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማ የሚሆነው ከባለድርሻ አካላት እና ከሕብረተሰቡ አስፈላጊው ትብብር እና ድጋፍ ሲሠጠው መሆኑን ገለጹ Print 2492