Thursday, April 6, 2023 / Categories: News የፍርድ ቤቱ አዲስ ተሿሚ ፕሬዝዳንቶች እና በቀድሞ ፕሬዝዳንቶች መካከል የስራ ርክክብ ተፈጸመ መጋቢት 27ቀን 2015 ዓ.ም፡- የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዲስ በተሾሙ ፕሬዝዳንቶች እና በቀድሞ ፕሬዝዳንቶች መካከል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳነት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት (ረዳት ፕሮፌሰር) በተገኙበት የስራ ርክክብ ስነስረዓት ተፈጸመ፡፡ከፍርድ ቤቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ብረሃነመስቀል ዋጋሪ የስራ ርክክቡን ያደረጉት የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 26ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው ሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ ሹመታቸዉን ያጸደቀው ክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ ናቸው፡፡የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት እንደ ገለጹት የስራ ርክክብ ሽግግር የሚደረግበት መሆኑን እና በተቋም ውስጥ ሰዎች ቢቀያየሩም ተቋም የሚቀጥል በመሆኑ ሁሉም የራሱን አሻራ ማኖር የሚገባው መሆኑን ጠቁመው፤ አብሮ የመስራት መንፈስን መገንባትና የፍርድ ቤቱን ስልጣን በማይነካ መልኩ አብሮ መስራት የሚያስፈልግና አመራሩም አስፈላጊዉን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሥራ ርክክብ ሥነ ሥርዓቱ የእንኳን ደህና መጣቹህ መልዕክት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዘዳንት ክቡር አቶ ተኽሊት ይመስል ያስተላለፉ ሲሆን፤ በመልዕክታቸው መርሃግብሩ የስራ ርክክብ ጊዜ መሆኑን በማንሳት የቀድሞ የስራ ኃላፊዎች ክቡር አቶ ብርሃነመስቀል ወጋሪ እና ክብርት ወ/ሮ ተናኘ ጥላሁን በኋላፊነት ዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ በማመስገን አዲስ ተሿሚወች መልካም የስራ ግዜ እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።የቀድሞ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ብርሃነመስቀል ወጋሪ በርክክብ ስነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ቀደም ሲል ለረዥም ዓመትት ያገለገሉ መሆኑን እና ለዚህም ከፍተኛ ደስታ የሚሰማቸው መሆኑን ገልጸው፣ አዲስ ተሽዋሚዎቹም ፍርድ ቤትን የሚያውቁና ጫናዎችን መቋቋም የሚችሉ ከመሆናቸዉም በተጨማሪ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ለማገዝ ያለው ቁርጠኝነት ደስታቸዉን እጥፍ እንደሚያደርገዉ ተናግረዋል፡፡ቀደም ሲል የተሰሩ ጥሩ ስራዎች እንዳሉ ሆነው ሳይሰሩ የቀሩ ክፍተቶች ካሉ አዲስ ተሽዋሚዎች የሚሞሉት መሆኑን ያነሱት ክቡር አቶ ብርሃነመስቀል፤ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባልተሟላ ሁኔታና ምቹ የሆነ የስራ ቦታና ችሎት በሌለበት ኃላፊነታቸውን ሲወጡ የቆዩ መሆኑን እና ይህን ልዩ የሆነ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ባህሪ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራር የሚረዳ በመሆኑ ፍርድ ቤት ይሻሻል የሚል ተስፋ ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡አዲስ የተሾሙት ፕሬዝዳንት ክብርት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ እንደተናገሩት አሁን ላይ ስራን በማስተላለፍ ርክክብ ማድረጉ የስራ ጫናን እና ሰዓትን የሚቆጥብ በመሆኑ በጣም ጥሩ መሆኑን አንስተው፤ ቀደም ሲል የተሰሩት ስራዎች ጥሩና አበረታች የነበሩና ለቀጣይነቱም ቀደም ሲል የነበሩ ክፍተቶች ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ መስራት የሚገባን ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግና ጥሩ የሆነ የቡድን ስራ ላይ ትኩረት ማድረግ የሚያሻው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ክብርት ፕሬዝዳንቷ አያይዘውም ፍርድ ቤቱ ካለው የስራ ጫናና ስፋት አንጻር ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ከመንግስት ድጋፍ ውጪ ስኬታማ መሆን ስለማይችል ተገቢዉ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡ በርክክብ ስነ-ስረዓቱ ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንትነት የተሾሙት ክብርት ወ/ሮ ዛህራ ኡመርም የተገኙ ሲሆን ከስነ-ስርዓቱ በኋላ የፍርድ ቤቱን ቅጥር ግቢ ጎብኝተዋል፡፡ክብርት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ለሌሴ ደሳለኝ ቀደም ሲል ከአራት አመታት በፊት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ተሹመው ያገለገሉ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ Previous Article ፍርድ ቤቱ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ያደረገው ስምምነት የፍርድ ቤቱን ማሕበረሰብ ጫና ለመቀነስና አገልግሎቱን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገለጸ Next Article አጣሪ ጉባዔው በአራት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ Print 1940