የፍርድ ቤቱ ዳኞች እና የአስተዳደር ዘርፍ የሥራ ክፍሎች በ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና በ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ግምገማ አካሔዱ
/ Categories: News

የፍርድ ቤቱ ዳኞች እና የአስተዳደር ዘርፍ የሥራ ክፍሎች በ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና በ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ግምገማ አካሔዱ

 

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኞች እና የአስተዳደር ዘርፍ የሥራ ክፍሎች በ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምና በ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከነሐሴ 4-7 ቀን 2014 ዓ.ም ግምገማ አካሄዱ፡፡

የፍርድ ቤቱ ዳኞች ነሐሴ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ያካሔዱት የአንድ ቀን የሥራ አፈጻጸም እና የዕቅድ ግምገማ የተመራው በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት በክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ሲሆን በመድረኩ ላይ የችሎቶች ዕቅድ አዘገጃጀትን የተመለከተ ማብራሪያም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በሌላ በኩል የፍርድ ቤቱ የአስተዳደር ዘርፍ 18 የሥራ ክፍሎች በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸማቸው እና በበቀጣዩ በጀት ዓመት ዕቅዳቸው ላይ ከነሐሴ 4-6 ቀን 2014 ዓ.ም ለሶስት ቀናት የቆየ ግምገማ አካሒደዋል፡፡

በፍርድ ቤቱ ስትራቴጅክ ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ዳኞች እና የአስተዳደር ዘርፍ የሥራ ክፍሎች ያካሔዱት የሥራ አፈጻጸምና የዕቅድ ዝግጅት ግምገማ ዋና ዓላማ የ2014 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ላይ በመወያየት ጠንካራ አፈጻጸሞችን ለማበረታታትና በቀጣዩ በጀት ዓመትም ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ፣ ባለፈው በጀት ዓመት የታዩ የአፈጻጸም ውስንነቶችን በ2015 በጀት ዓመት እንዲታረሙ ለማድረግ እንዲሁም በሚቀጥለው በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ለተግባራዊነቱ ለመንቀሳቀስ ነው፡፡

የዳኝነት ዘርፉን የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጻም አስመልክቶ በቀረበው ማብራሪያ ላይ በ2014 በጀት ዓመት ለሶስቱም ፌደራል ፍርድ ቤቶች ማለትም ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት፣ ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት እና ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በአጠቃላይ ከቀረቡ 209,317 መዛግብት ውስጥ 176,797 መዛግብት ዕልባት ያገኙ መሆኑና 32,520 መዛግብት ደግሞ ለ2015 በጀት ዓመት የተላለፉ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የፍርድ ቤቶቹ አፈጻጸም ከዕቅድ አንጻር ዚመዘን ደግሞ በሶስቱም ፌደራል ፍርድ ቤቶች በ2014 በጀት ዓመት ዕልባት ለመስጠት በዕቅድ የተያዘው 187,710 መዛግብት ሲሆን በተጠቀሰው ጊዜ 176,797 መዛግብት ዕልባት በማግኘታቸው አፈጻጸሙ 94.2 በመቶ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የአስተዳደር የሥራ ክፍሎች ባደረጉት ውይይት ማጠቃለያ ላይ በ2014 በጀት የሥራ አፈጻጸም በጠንካራ ጎንነት ከተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል የሥራ ክፍሎች ከጥቃቅን ሥራዎች ወጥተው ስትራቴጅካዊ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ መጀመራቸው፣ በተጠቀሰው ጊዜ ከአንድ መስኮት አገልግሎት ጋር በተያያዘ በሬጅስትራር የሥራ ክፍል ቀልጣፋና ግልጽነት ያለው ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑ፣ የዳኝነት አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ በተደገፈ ሁኔታ ቀልጣፋና ተደራሽ እየተደረገ መምጣቱ እንዲሁም ፍርድን ከማስፈጸም አኳያ ግልጽ፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚደረገው ጥረት እንደአበረታች ውጤት ተጠቅሰዋል፡፡

በተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት በመደረግ ላይ ያለው ጥረት፣ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ሥራዎችን በቂ የሰው ኃይል በሌለበት ተፈጻሚ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት፣ በግብአት አቅርቦት፣ በንብረት አያያዝ፣ በነዳጅ አጠቃቀም፣ በፋይናንስ የሥራ ክፍል እና የግዥ አፈጻጸም በዓመቱ መጨረሻ ከተለመደው የጥድፊያ አሠራር ወጥተው ሥራቸውን ዕቅድን መሠረት በማድረግ ማከናወናቸው መሻሻል የታየበት መሆኑ በውይይቱ ላይ እንደጠንካራ ጎን ተነስቷል፡፡

በዕቅድ ክንውን አፈጻጸሙና በዕቅድ ግምገማው ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ፕሬዚደንትን ጨምሮ የፍ/ቤቱ ዳኞች፣ የፍ/ቤቱ የፕሬዚደንትና የም/ፕሬዚደንት ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ ኮርት ማኔጀር፣ ዋና ሬጅስትራር፣ የየሥራ ክፍሎቹ ዳይሬክተሮች እና ቡድን መሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡

የፌደራል ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ፍርድ ቤቱ ሐሰተኛ የቃለ-መሐላ አቤቱታ ያቀረቡ ባለጉዳይን በችሎት መድፈር እንዲቀጡ ወሰነ
Next Article ዳኞች በማያቋርጥ ሒደት ብቃታቸውን ሊያሳድጉና በሥልጠና ሊያልፉ እንደሚገባ ተጠቆመ
Print
398