የፍርድ ቤት መር  አስማሚነት ላይ የሁለት ቀናት ስልጠና ተሰጠ
/ Categories: News

የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ላይ የሁለት ቀናት ስልጠና ተሰጠ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፌደራል የፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት እና ከኢትዮጵያ የማስማማትና ግልግል ዳኝነት ማዕከል (EMAC) ጋር በመተባበር የሁለት ቀናት ስልጠና ለፌደራል ከፍተኛ እና መጀመሪያ ፍርድ ቤት ረዳት ዳኞች ተሰጥቷል፡፡

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የፌደራል ፍርድ ቤት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ፅ/ቤት ሃላፊ ክቡር ዳኛ አበበ ሰለሞን የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ተከራካሪ ወገኖች መሀል ያለው ግኑኝነት ተጠብቆ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍቻ ዘዴ እንደመሆኑ ከፍትሕ ስርአት ማስከበር አኳያ ትልቅ አሰተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

አክለውም ተከራካሪ ወገኖች የይቅር ባይነትን ስሜት በማዳበር እና የማህበረሰባዊ ዕሴቶችን ባስጠበቀ መልኩ ችግሮቻቸውን መፍታት እንዲች ያግዛል ብለዋል፡፡

በፌደራል የፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት የዳኝነት ማስተባበሪያ ዴስክ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ታለ በፍርድ ቤት መር አስማሚነት ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና መሰጠቱ ያለውን ጠቀሜታ እና ጉልህ ሚና ገልፀው፤ ስለ አጠቃላይ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት መርሆዎችና ተያያዥ ጉዳዮች አንስተዋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የፌደራል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ዘካርያስ ኤርኮላ በበኩላቸው የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ለተከራካሪ ወገኖች ካለው ጠቀሜታ ባለፈ በፍርድ ቤቶች ያለውን የመዝገቦች መደራረብን የሚቀንስ መሆኑን አንስተው ሰልጣኞችም የማስማማት ስራ በሚያከናውኑበት ወቅት ሙያው የሚፈልገውን ስነ ምግባር በመላበስ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኮሚኒኬሽንና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ዳይሬክቶሬት

Previous Article ስዊድን አገር ለተደረገው የስራ ጉብኝትና ልምምድ ልውውጥ ስኬት ላበረከቱ አካላት የምስጋና መርኀ ግብር ተካሄደ፡፡
Next Article በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ አምባሳደር ክቡር ሚ/ር አሌክስ ላሜክ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት አደረጉ
Print
794