የፍርድ ቤት ተገልጋዮችን እንግልት የሚቀንሱ እና የፍትሕ እርካታ የሚጨምሩ የማሻሻያ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተገለጸ
/ Categories: News

የፍርድ ቤት ተገልጋዮችን እንግልት የሚቀንሱ እና የፍትሕ እርካታ የሚጨምሩ የማሻሻያ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተገለጸ

የፍርድ ቤት ተገልጋዮችን ጊዜ፣ ጉልበት እና የገንዘብ ወጪ የሚቀንሱ እና የፍትሕ እርካታ የሚጨምሩ የማሻሻያ ሥራዎች የሚከናወኑ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ገለጹ፡፡
ፍርድ ቤቱ እና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት መጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ተፈራርመዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ ዓላማ የፈደራል ፍርድ ቤቶችን ተገልጋዮች እንግልት መቀነስ፤ የቀረጥ ቴምብር እና ተመሳሳይ ከኢትዮጵያ ፖስታ የሚቀርቡ ቁሶችን ጠበቆች፣ ፍርድ ቤቶቹ እንዲሁም ተገልጋዮች ያለ እንግልት እንዲያገኙ ማስቻል፤ ሰነዶች ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲዘዋወሩ ማድረግ እና የፈዴራል ፍርድ ቤቶች ወጪ ቆጣቢ የሆኑ ሌሎች አገልግሎቶችን ከድርጅቱ እንዲያገኙ ማስቻል ነው፡፡
በፊርማ ሥነሥርዓቱ ላይ ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት ባደረጉት ንግግር የመግባቢያ ስምምነቱ በፍርድ ቤቶች የሚፈለጉና ከአንድ ፍርድ ቤት ወደሌላ ፍርድ ቤት የሚንቀሳቀሱ መዛግብትን በጥንቃቄ ለማጓጓዝና በፖስታ ቤት የሚሰጡ ሌሎች አገልግሎቶችን የፌደራል ፍርድ ቤቶች ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ጠቁመው፣ ይህም ለደንበኞች የተሻለ አገልግሎት እና እርካታ እንደሚያስገኝ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ወደፊትም የተገልጋዮችን እርካታ ሊጨምሩ የሚችሉ ሌሎች አገልግሎቶችን ከድርጅቱ ማግኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሁለቱ ተቋማት አጋር እንደሚሆኑ ጠቁመው፣ የስራ ክንውኖችን በየጊዜው በመገምገም፣ የጎደሉትን በማሻሻልና ጥንካሬዎችን በማስቀጠል አብረው እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡
የፍርድ ቤቱ ሰነዶች በጣም ጥንቃቄ የሚፈልጉ መሆኑን በማስገንዘብም በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በኩልም ከፍተኛ ትጋትና ጥንቃቄ ሊኖር እንደሚገባ አሳስበበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሀና አርአያስላሴ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ፍርድ ቤቱ የተሻለ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት እያደረገ ባለው የለውጥ ሥራ አካል በመሆናቸው ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመው በፍርድ ቤቱ በኩል ድርጅታቸው የተጣለበትን ታላቅ አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንና ለዚህም በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የፈደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተመሳሳይ ሁኔታ ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በቴክኖሎጂ ዘርፍ አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም የተፈራረመ መሆኑ ይታወሳል።
Previous Article ፍርድ ቤቱ እና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ
Next Article ፍርድ ቤቱ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ያደረገው ስምምነት የፍርድ ቤቱን ማሕበረሰብ ጫና ለመቀነስና አገልግሎቱን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገለጸ
Print
1681