የፍ/ቤቱ ዳኞች በጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር እና በመዛግብት አፈጻጸም ዙሪያ አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸው ተገለጸ
/ Categories: News

የፍ/ቤቱ ዳኞች በጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር እና በመዛግብት አፈጻጸም ዙሪያ አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸው ተገለጸ

ፍርድ ቤቱ 20 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ከመንግስት ማግኘቱም ተጠቁሟል

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በ2014 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደርን ተግባራዊ በማድረግ እና በመዛግብት አፈጻጸም ያስመዘገቡት ውጤት አበረታች በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው የፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ገለጹ፡፡

ክብርት ፕሬዚደንትዋ ይህን የገለጹት የፍርድ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳኞች እና ረዳት ዳኞች በተሳተፉበትና በፌደራል ፍ/ቤቶች የአምስት ዓመታት (2014-2018 ዓ.ም) ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ዋና ዋና ይዘት እና በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የችሎቶችና ዳኞች የ2014 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የመዛግብት አፈጻጸም ላይ መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል የተደረገውን ውይይት ሲያጠቃልሉ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

በመዛግብት አፈጻጸምም ሆነ በፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ዳኞች ላስመዘገቡት ውጤት ምስጋናቸውን ገልጸው ባለፉት ስድስት ወራት የተመዘገበው ውጤት ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ለውይይቱ ተሳታፊ ዳኞችና ረዳት ዳኞች ገልጸዋል፡፡

የመዛግብት አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ አንጻር‚ በንጽጽር ሲቀርብም  በ2013 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት 11‚224 መዛግብት ቀርበው 5‚860 መዛግብት ዕልባት ያገኙ ሲሆን በ2014 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት 14‚231 መዛግብት ለፍ/ቤቱ ቀርበው 8‚145 መዛግብት ዕልባት ያገኙ በመሆኑ ዘንድሮ 3‚007 መዛግብት በተጨማሪነት መቅረባቸውንና ለተጨማሪ 2‚285 መዛግብት ዕልባት መሰጠቱ ተጠቅሷል፡፡ 

የ2014 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የመዛግብት አፈጻጸም ዕቅድ 6‚776 ሲሆን የተመዘገበው አፈጻጸም 8,145 በመሆኑ የተመዘገበው ውጤት 120.2% እንደደረሰ በውይይቱ ላይ ቀርቧል፡፡ እልባት ካገኙት መዛግብት መካከል 94 በመቶ የሚሆኑትም በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ዕልባት ያገኙ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

በፍርድ ቤቱ ችሎቶች በመታየት ላይ ያሉ መዛግብት ሁኔታ በዝርዝር ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ካላፈው በጀት ዓመት የተዛወሩ መዛግብት የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደርን በተሻለ ሁኔታ ለመተግበር ዋና እንቅፋት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ መረጃ በዳታ ቤዝ ያልገባላቸውና የተንጠለጠሉ ጉዳዮች ፍርድ ቤቱ በሚሰጠው አገልግሎት የባለጉዳዮችን እርካታ መቀነስና እንግልት መጨመር ምክንያት ሆኗል ተብሏል በቀረበው ሪፖርት፡፡ 

የቀረበውን ሪፖርት መሰረት በማድረግ የተካሄደውን ውይይት የመሩት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በበኩላቸው የሚሻገሩ መዛግብት የሚከፈለውን መስዋዕትነት በመክፈል በአጭር ጊዜ እልባት ካልተሰጠባቸው ችግሩ የሚቀጥል መሆን አሳስበው በቀሪው ጊዜ የተዛወሩ መዛግብትን እያበሰሉ በክረምቱ ጊዜ ውሳኔ በመስጠት የተሸጋሪ መዛግብት ቁጥርን ለመቀነስ ዳኞች መትጋት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

ከተንጠለጠሉ መዛግብት ጋር በተያያዘም ችግሩ መረጃ በመረጃ ቋት ውስጥ ከሚስገቡ ባለሙያዎች እና ከኢንተርኔት መቆራረጥ ሊመነጭ እንደሚችል የሚታሰብ ቢሆንም መዛግብት ያለቀጠሮ በዳኞች እጅ መቆየታቸው አንዱ ምክንያት ሊሆን  ይችላል ብለዋል፡፡ ስለሆነም በተለያየ ምክንያት መዛግብት በዳኞች እጅ እንዲቆዩ የሚያስፈልግበት ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ አጭር ቀጠሮ በመስጠት መረጃው ወደ ዳታ ቤዝ ገብቶ መዝገቡ እንዲመለስላቸው የሚያስችል አሰራር መዘርጋት አንዳለባቸውም ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡ 

ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በውይይት መድረኩ የፍርድ ቤቱን ደረጃ የጠበቀ ህንጻ ለመገንባት የሚያስችል ቦታ ለማግኘት ለመሬት አስተዳደር መስሪያ ቤቶች ጥያቄ ቀርቦ ተደጋጋሚ ወይይት እየተደረገ መቆየቴን አስታውሰው የፍርድ ቤቱ አመራር ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባደረገው አጭር ወይይት ጉዳዩን በተገቢው ማስረዳት በመቻሉና መንግስትም ልዩ ትኩረት በመስጠት በአጭር ጊዜ በከተማችን መሃል 20 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መሬት ወሎ ሰፈር አካባቢ ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡  የመሬት ርክክቡም በቅርቡ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡   

የፌደራል ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በፓናል ውይይት አከበሩ
Next Article ፍርድ ቤቱ የዲጂታል የሀብት ማስመዝገብ መርሐ-ግብር አስጀመረ
Print
140