የ2014 አዲስ ዓመት ጅማሬን አስመልክቶ ከጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ለፌደራል ፍ/ቤቶች ዳኞች የተላለፈ የምስጋና መግለጫ
ክቡራንና ክቡራት ዳኞች
ያጠናቀቅነው የ2013 ዓ.ም በፍርድ ቤታችን ጉልህ የሚባሉ የማሻሻያ ሥራዎች የተከናወኑበትና በዚህ ረገድ በቀጣይ ለሚመዘገቡ ስኬቶች መሠረት የተጣለበት ሆኖ የሚወሰድ ነው፡፡
ባሳለፍነው ዓመት ለፍርድ ቤቱ የማሻሻያ ሥራ መሠረታዊ ከሆኑት እና በፍርድ ቤቶች የዳኞችን እና ተቋማዊ ነጻነትን፣ ገለልተኝነትን እንዲሁም ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል የተሻሻሉት የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ እና የፌደራል የዳኝነት አስተዳደር አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፀድቀው ወደሥራ መግባታቸው ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ነው፡፡
እነዚህን አዋጆች ተግባራዊ ለማድረግም በርካታ ደንቦችና መመሪያዎች እየተዘጋጁና እየጸደቁ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ መካከል የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ እና የዳኞች ሥነምግባር እና የዲሲፒሊን ሥነሥርዓት ደንብ የፀደቁ ሲሆኑ በቅርቡ ፀድቀው ወደትግበራ እንደሚገቡ ከሚጠበቁት መካከል የአስተዳደር ሰራተኞች መተዳደሪያ ደንብ እና የዳኞች የሥራ አፈጻጸም ምዘና መመሪያ ይጠቀሳሉ፡፡
በዚህ ዓመት ከተከናወኑና መጠቀስ ከሚገባቸው የፍርድ ቤቱ መደበኛ ሥራዎች መካከል የፍርድ ቤቶቻችን የመዝገብ አፈጻጸም አንዱ ነው፡፡ በሶስቱም የፌደራል ፍርድ ቤቶች ለ171,276 መዛግብት እልባት ተሰጥቷል፡፡ ይህም ከተያዘው ዕቅድ አንጻር የፍ/ቤቶችን የመዝገብ አፈጻጸም 102.7 በመቶ አድርሶታል፡፡
እልባት ካገኙ መዛግብት መካከል 150,283 መዛግብት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እልባት ያገኙ ሲሆን ይህም 87.74 በመቶ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በመዝገብ አፈጻጸም ረገድ ለነበረው ውጤታማነት በዋናነት የክቡራን ዳኞቻችን አበርክቶ ከፍተኛ ድርሻ የነበረው ሲሆን ለውጤቱ መመዝገብ የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞቻችን አስተዋጽኦም ተገቢው ግምት የሚሰጠው ነው፡፡
ፍርድ ቤቶቻችን ከምርጫ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ፈጣንና ጥራት ያለው ውሳኔ ለመስጠት ሰፊ ዝግጅት ያደረጉ ቢሆንም በሶስቱም ፍርድ ቤቶች 74 ጉዳዮች ቀርበው ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ይህም በአገራችን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሔድ ፍርድ ቤቶቻችን የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ስለማድረጋቸው ማሳያ ነው፡፡
የተከበራችሁ ዳኞች
በፌደራል ፍርድ ቤቶቻችን የዳኝነትን ግልጽነት ከማረጋገጥ አኳያም የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በዚህ መሠረት በሁሉም ፍርድ ቤቶች የሚታዩ የማስቻያ ቦታ እጥረቶችን ለማቃለል ችሎቶች በፈረቃ መጠቀም የሚችሉበት መርሃ ግብር በማውጣት፤
ተጨማሪ የችሎት አዳራሾችና እስቴጆችን በማደራጀት የዳኝነት አገልግሎት በግልጽ ችሎት እንዲሰጥ ጥረት ተደርጓል፡፡ በተለይም በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎቶች የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በማደራጀት እና በማስፋፋት ተገልጋዮች ከችሎት ውጪ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ እና በግልጽ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት እንዲያገኙ ለማድረግ የተከናወነው ሥራም ተጠቃሽ ነው፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፌዴራል ጉዳዮችን እንዳይመለከቱ ውክልና በተነሳባቸው ክልሎች ዳኝነት የሚሰጡ የተዘዋዋሪ ችሎቶችን ቁጥር ከሁለት ወደ ስድስት ከፍ በማድረግ በ15 ዳኞች የዳኝነት አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተደራሽነቱን ለማስፋት የሃዋሳ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማዕከልን በማቋቋምና አስፈላጊው ግብአት ተሟልቶለት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በአርባ ምንጭ ከተማ ተመሳሳይ ማዕከል ለማደራጀት እያደረገ ያለው ጥረትም ተስፋ ሰጪ ውጤት አስገኝቷል፡፡
የዳኝነት አገልግሎትን በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በማስደገፍ በበጀት ዓመቱ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚገኙ አምስት ችሎቶች የICT ውጤት የሆኑ ዲጂታል የደምጽና የምስል መቅረጫ መሳሪያዎች ከማይክ፤ ካሜራ እና ስክሪን ጋር እንዲገጠምላቸው በማድረግ ባለጉዳዮች በችሎት ውስጥና ውጪ የችሎት ሂደቱን እንዲከታተሉ በማድረግ የዳኝነት ግልጽነትን ማጠናከር ተችሏል፡፡ በከፍተኛ ፍርድ ቤት አምስት ምድብ ችሎቶችም የቪዲዮ ኮንፈረንስ መሳሪያዎች የተገጠመላቸው በመሆኑ የፍ/ቤቱን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ ለማድረግ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ከዚህ አኳያ በክልል ፍርድ ቤቶችና ማረሚያ ቤቶች በቪዲዮ ኮንፈረንስ የተደራጁ 46 የርቀት ችሎት ማዕከላትን በመጠቀም በ2,284 መዛግብት ለተከሰሱ 3,751 ባለጉዳዮች ጉዳዮቻቸውን በቪዲዮ ኮንፈረንስ እንዲከታተሉ ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይም በዘጠኝ ክልሎች የኢ-ፋይሊንግ ማዕከላትን በማስፋፋት 1,737 የይግባኝና የሰበር መዛግብትን ማስተናገድ ተችሏል፡፡ የዳኝነት አገልግሎቱ በቪዲዮ ኮንፈረንስ እና በኢ-ፋይሊንግ አማካኝነት የታገዘ እንዲሆን በመደረጉ ምክንያት ተገልጋዮች አዲስ አበባ በመምጣት ሊደርስባቸው የሚችለውን ድካም፣ እንግልትና ጊዜ ከመቀነስ ባሻገር ሊያወጡት የሚችሉትን ብር 11,620,000 ማዳን ችለናል፡፡
ከዚህ በላይ በከፊል ከተጠቀሱት የ2013 ዓ.ም የፍርድ ቤቶቻችን ስኬቶችና አፈጻጸሞች በስተጀርባ የክቡራን ዳኞቻችን ትጋትና ውጤታማነት የማይተካ ሚና የነበረው ስለመሆኑ በዚህ አጋጣሚ መግለጽ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም በፍርድ ቤቶቻችን እስካሁን ተግባራዊ በተደረገው የማሻሻያ ሥራ ላይ ዳኞቻችን የበኩላቸውን ተሳትፎ ለማድረግ ያሳዩት ታታሪነትና ቅንነት እስከአሁን ለተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበረው በመሆኑ ለክቡራን ዳኞቻችን ከፍ ያላ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
ውድ ዳኞች በመጨረሻም
በአሁኑ ወቅት የፍ/ቤታችን የማሻሻያ ሥራዎች ከፍ/ቤቶች ውጭ ባሉ አካላትም ዕውቅና እያገኘ በመምጣት ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በቅርቡ የፀደቀውን የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ተፈጻሚ በማድረግ ፍርድ ቤቶቻችን የሚወቀሱበትን በተደጋጋሚ ቀጠሮ ሊኖር የሚችልን አንግልት በመቀነስ ጉዳዮች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እልባት እንዲያገኙ በቀጣዩ ጊዜ በትጋትና በታታሪነት እንድንንቀሳቀስ አደራ እላለሁ፡፡
በአዲሱ ዓመት የዳኝነት ሙያዊ ነጻነትን፣ ገለልተኝነትን እና ተጠያቂነትን በላቀ ደረጃ ተፈጻሚ በማድረግ፣ በከፍተኛ የዳኝነት ሥነምግባር በመመራት ቀሪ የፍርድ ቤቶቻችንን የሪፎርም ሥራዎች በማስቀጠል የፍርድ ቤቶቻችንን ተገልጋዮች እርካታ ከመቸውም ጊዜ በላይ የምናሳድግበትና ሕብረተሰቡ በፍርድ ቤቶቻችን ላይ ያለውን አመኔታ ከፍ የምናደርግበት ዘመን እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡
መልካም አዲስ ዓመት!
አመሰግናለሁ!
476