ዳኞች ስራ ላይ ባሉ ህጎችና ፋይዳቸው ላይ የጽሁፍ ውጤቶችን ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ
ዳኞች ስራ ላይ ባሉ ህጎችና ፋይዳቸው ላይ የጽሁፍ ውጤቶችን ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ ዳኞች በስራ ላይ ባሉ ህጎችና ፋይዳቸው ላይ ጥናትና ምርምር በማካሄድ የጽሑፍ ውጤቶችን ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው ገለጹ፡፡
አቶ ሰለሞን አረዳ ይህን የገለጹት በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት በሆኑት በክቡር አቶ ተስፋዬ ነዋይ “የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ሕጋዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ” በሚል ርዕስ የታተመ መጽሐፍ የምረቃና የትችት መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡
ጸሐፊው ዕረፍት በማይሰጥ የመንግስት ኃላፊነት ላይ የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ ባለፉት ሶስት ዓመታት ሶስት መጽሐፍትን ጽፈው ለህትመት ማብቃታቸው ለፌዴራል ዳኞች ትልቅ አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን የተናገሩት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ ዳኞች የመዝገብ ጫና ያለባቸው ቢሆንም ጊዜያቸውን ቆጥበው በሙያቸው ጥናትና ምርምር በማካሄድ ውጤቶቻቸውን በመጽሐፍ መልክ በማቅረብ ለማህበረሰቡ እውቀታቸውን ማካፈል ይችላሉ ብለዋል፡፡
በመጽሐፍ ምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የተሳተፉ ዳኞች በሰጡት አስተያየት ክቡር አቶ ተስፋዬ የፍርድ ቤት አመራር ሆነው በኢኮኖሚውና በህጉ ዘርፍ ትስስር በሚፈጥር ጉዳይ ላይ አስተማሪ የሚሆን መጽሐፍ ጽፈው ማሳተማቸው ቀላል እንዳልሆነ ገልጸው ዳኞች ለሚቀርቡላቸው በርካታ ጉዳዮች ዳኝነት ከመስጠት ባሻጋር ሌሎች የጎንዮሽ ስራዎችን መስራት እንደምንችል ተምሳሌት አድርገን የምንወስደው ነው ብለዋል፡፡ አቶ ተስፋዮ የፍርድ ቤት አመራር በመሆናቸው ኩራት እንደሚሰማቸው እና ለእርሳቸው ክብርም እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
የመጽሐፉ ምረቃ ፕሮግራም ከህግ ባለሙያዎች ማህበር በተገኘ ድጋፍ የተዘጋጀ ሲሆን በመድረኩ የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትር ሚኒስቴር ድኤታ አቶ ሐሰን መሃመድ ፣ የህግ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝደንት አቶ ፊሊፖስ ዓይናለም፣ እና የደራሲያን ማህበር ም/ሊቀመንበር ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ መጽሐፉ በሸማቾች፣ በንግድ ስርዓቱ ፣ በህግና በኢኮኖሚው ዘርፍ በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
134